በኢትዮጵያ ግዙፉ የብሄራዊ ስታዴየም የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በመገባደድ ላይ ነው

1320

አዲስ አበባ ጥቅምት 18/2011 በኢትዮጵያ በትልቅነቱ ቀዳሚ የሆነው ብሄራዊ ስታዲየም  የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ በመገባደድ ላይ መሆኑ ተገለፀ።

“አደይ አበባ” የሚል ስያሜ በመሃል አዲስ አበባ እየተገነባ ያለው ስታዲየሙ  የመጀመሪያው ምእራፍ ግንባታ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በቻይናው ”ስቴት ኮንስትራክሽን” ኢንጅነሪንግ ኩባንያ የሚገነባው ብሄራዊ ስታዲየም  62 ሺህ ሰዎችን በወንበር የመያዝ አቅም አለው።

የስታዲየሙ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ የሚካሄደው በ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በጀት ነው።

ግንባታው በታህሳስ 2008 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን  ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር።

ይሁን እንጂ  በዝናብ ወቅት እንደልብ ለመስራት ባለመቻሉና ከውጭ በሚገቡ እቃዎች በጊዜው ባለመድረሳቸው የተነሳ እንደዘገየ ተገልጿል።

የውጭ ምንዛሬ እጥረት ስራው ላይ ጫና እንዳሳደረም ተገልጿል።

ግንባታውን  እያከናወነ የሚገኘው የቻይናው ”ስቴት ኮንራክሽን” ዋና ኢንጅነር ሚስተር ቹ ኩንጃዩ የስታዲየሙ ዋና ስትራክቸር ተጠናቋል ብለዋል።

የስታዲየሙ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራ በአሁኑ ወቅት ከ90 በመቶው በላይ ተጠናቋል ያሉት ዋና ኢንጅነሩ አሁን በዋናነት የቀረው ስራ የስታዲዮሙ የሜዳ ክፍል እንደሆነ ነው የገለጹት።

በመጀመሪያው ምዕራፍ የተካተቱት የተጫዋቾች የልብስ መቀየሪያ ክፍልና የመፀዳጃ ቤት የኮርኒስ ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነ ተናገረዋል።

ዋና ኢንጂኒየሩ እንደሚሉት የስታዲየሙ የመጀመሪያ ምዕራፍ ስራ እስከ መጪው ታህሳስ ወር ይጠናቀቃል።

የእግር ኳስ ሜዳው ግን ተፈጥሮዊ ሳር የሚተከልበት በመሆኑ እሱን ለንመከባከብ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ እስከ ሚያዚያ 2011 ዓ.ም ሊቆይ ይችላል ነው ያሉት።

በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር የግንባታው ተቆጣጣሪ አቶ ጥበቡ ጎርፉ የመጀመሪያውን ዙር ግንባታ እስከ ታህሳስ መጨረሻ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ግንባታው ባለፈው አመት በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ መዘግየት እንዳጋጠመው አንስተዋል።

የስታዲየሙ ግንባታ ሲጠናቀቅ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮችን ከማስተናገድ በተጨማሪ ሌሎች እንደ አትሌቲክስ አይነት ውድድሮችን ለማስተናገድ ምቹ አጋጣሚን የሚፈጥር ነው።