መንግስት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን ጠብቆ ለትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነቱን ይወጣል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ

1385

ባህር ዳር ጥቅምት 18/2011 ”አባቶቻችን በረቀቀ እውቀትና ጥበብ የሰሩዋቸው የላሊበላ የውቅር አብያተ ክርስትያናት ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ የማድረግ ኃላፊነት አለብን” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ላይ የደረሰውን ጉዳት በቦታው በመገኘት ተመልክተዋል።

በመድኃኔ አለም ዓውደ ምህረት ባደረጉት ንግግርም ”የአገራችን መገለጫ የሆነውን ቅርስ ለመጠገንና ለትውልድ ጠብቆ ለማቆየት መንግስት ኃላፊነቱን ይወጣል” ብለዋል።

የፌዴራል መንግስት ከክልሉ መንግስትና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን  ጋር በመተባበር አፋጣኝ መፍትሄ ለማፈላለግ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናግረዋል፡፡

የላሊበላ ከተማ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ላደረገው ደማቅ አቀባበል ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ምስጋና አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድና የፌዴራልና የአማራ ክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች  የቤተ መድኃኔ አለም እና የቤተ ማርያም ውቅር አብያተ ክርስትያናትን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና ሌሎች የክልሉና የፌዴራል  መንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።