ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝትወደ ፈረንሳይ ሊያቀኑ ነው

71
አዲስ አበባ ጥቅምት 18/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ነገ ወደ ፈረንሳይ ያቀናሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፈረንሳይ ቆይታቸው ከአገሪቷ ፕሬዝዳንት ማኑኤል ማክሮን ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ ለኢዜአ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፈረንሳይ ጉብኝታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ጀርመን እንደሚያመሩና ከጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጋር በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ እንደሚመክሩም ተናግረዋል። አቶ ፍጹም እንዳሉት ዶክተር አብይ ጉብኝቱን የሚያደርጉት ከአገሮቹ መሪዎች በቀረበላቸው ግብዣ መሰረት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ በአውሮፓ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት ያደርጋሉ። ጉብኝቱ የኢትዮጵያን የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲና የሁለትዮሽ ውጭ ግንኙነትና ትብብር ያጠናክራል ተብሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም