ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራው በተፈጠረው የህዝብ ንቅናቄ ልክ ውጤት አልተገኘም- ዶክተር ገመዶ ዳሌ

101
ሀዋሳ ግንቦት 14/2010 በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራው ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ንቅናቄ መፍጠር ቢቻለም  በዚህ ልክ ውጤት እንዳልተገኘ  የአካባቢ  ደን ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ዶክተር ገመዶ ዳሌ አስታወቀ፡፡ በአዲሱ የደን አዋጅ ዙሪያ በደቡብ ህዝቦች ክልል ለሚገኙ  ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተካሄዷል፡፡ በመድረኩ የተገኙት ሚኒስትሩ እንዳሉት አገሪቱ በምትከተለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጅ ውስጥ የደን ሃብቱ የልማቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚረዳ ነው፡፡ "እስካሁን በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራው ከፍተኛ የህዝብ ንቅናቄ መፍጠር ቢቻልም  በንቅናቄውና በሚወጣው ሃብት ልክ ውጤት አልተገኘም "ብለዋል፡፡ የዚህ ችግር በጥናት መለየቱን ያመለከቱት  ሚኒስትሩ የአመራሩና የፈጻሚው ግንዛቤ ማነስ ቀዳሚው ክፍተት በመሆኑ መድረኩ ይህንን ለመፍታት ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ባለድርሻዎች በተለይም የፍትህና ጸጥታ አካላት በአዲሱ ደን አዋጅ ላይ በቂ ግንዛቤ ይዘው በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለበቸውም ጠቁመዋል፡፡ የደን ዘርፍ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ያለው ፋይዳን በተመለከተ በመድረኩ ጽሁፍ ያቀረቡት በሚኒስቴሩ ብሄራዊ ሬድ ፕላስ  ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር ይተብቱ ሞገስ በበኩላቸው በሀገሪቱ ተራራማ ቦታዎችን በተገቢው ማልማት በሚያስችል መልኩ ፖሊሲ መቀረጽ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ አስተባባሪው እንዳሉት ተራሮች በደን ሲሸፈኑ መስኖና ኃይል ማመንጨት የሚችሉ ወንዞች፣ ለቱሪዝም ሃብት የሚሆኑ አረንጓዴ ስፍራዎችን በመገንባት ኢኮኖሚውን መደገፍ ይቻላል፡፡ "ለዚህም በመሰረታዊ ችግሩ ላይ መስራት ያስፈልጋል " ያሉት አስተባባሪው  በየዓመቱ 19 ሺ ሄክታር ደን ቢለማም 92 ሺ ሄክታር ደን በተለያየ ምክንያት እንደሚጠፋ ጠቅሰዋል፡፡ አዲሱ የደን አዋጅ ከዚህ ቀደም ለመንግስትና ለግለሰብ ብቻ የተሰጠውን የደን ባለቤትነት የቀየረ  መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሚኒስቴሩ የፖሊሲ ህግና ደረጃዎች ቻርተር ዝግጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር አየለ ሄጌና ናቸው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በዚህ መልኩ ልማቱን ማስቀጠል ስለማይቻል የማህበረሰብና የማህበራት ደን መካተቱን አስታውቀዋል፡፡ በዘርፉ ለሚሰማሩ ማህበራት ባለሃብቶችም ሆነ የህብረተሰብ ክፍሎች ማበረታቻ በአዋጁ መቀመጡን ጠቅሰው " መሬትን ከሊዝ ነጻ እንዲያገኙና በመጀመሪያዎቹ ሁለት ምርት ዘመንም ከገቢ ግብር ነጻ እንዲሆኑ ያደርጋል" ብለዋል፡፡ ህጉን ማዘመኑ ውጤታማ እንደሚያደርግ የገለጹት ዶክተር አየለ ለአዋጁ አፈጻጻም እስከታችኛው የመንግስት መዋቅር በትኩረት መስራት እንደሚኖርበትም አመልክተዋል፡፡ የደቡብ ህዝቦች ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ቃቀቦ  በበኩላቸው አዲሱ የደን አዋጅ በዘርፉ ለሚሰሩ ባለሃብቶች ማበረታቻ የሚሰጥና የማህበረሰቡን ሚና በማጠናከር የደን ዘርፉን በስፋት የዳሰሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ነባር ደኖችን የመጠበቅና የመንከባከብ፣ በየአካባቢው ያሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ደኖችን የመለየት፣ የመመዝገብና በየደረጃው ባሉ ምክር ቤቶች እውቅና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ "የተራቆቱ መሬቶችን በመከለል መልሶ እንዲያገግሙ በማድረግ የደን ሽፋኑን በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ  የትግበራ ዘመኑ መጨረሻ ወደ 25 በመቶ ለማሳደግ ይሰራል "ብለዋል፡፡ ከትናንት ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምክክር መድረክ በክልሉ የሚገኙ የዞን አስተዳዳሪዎች፣ የፍትህና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም