በአንኮበር በ4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ሙዚዬም ሥራ አለመጀመሩ ገቢያቸውን እንደቀነሰባቸው ባለሀብቶች ገለጹ

77
ደብረ ብርሃን ጥቅምት 17/2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአንኮበር ወረዳ በ4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ሙዚዬም ሥራ አለመጀመሩ ገቢያቸው እንዳሳነሰባቸው  ባለሀብቶች ገለጹ። የወረዳው አስተዳደር በበኩሉ  ሙዚዬሙ ሥራ ያልገባው በበጀት እጥረት ነው ይላል። ባለሀብቶቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳመለከቱት ሙዚዬሙ ከአንድ ዓመት በላይ ሥራ ባለመጀመሩ ጎብኚዎች በሚፈለገው መጠን ወደ አካባቢው እንዳይመጡ ተጽዕኖ አሳድሯል። ይህም በተሰማሩበት የንግድ ሥራ የጠበቁትን ያህል ገቢ  እንዳያገኙ ማድረጉን ተናግረዋል ። ከባለሀብቶቹ መካከል ኢንጂነር ተረፈ ራስ ወርቅ  በወረዳው ያለውን ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ተፈጥሮአዊ መስህቦች  ግምት ውስጥ በማስገባት በቱሪዝም ኢንቨስትመንት መስክ መሰማራታቸውን ይናገራሉ። የአንኮበር ቤተ-መንግሥትን በሊዝ ተረክበው በማልማት አካባቢውን ለጎብኚዎች ለማመቻቸትና ራሳቸውም ተጠቃሚ እንዲሆኑ30 የእንግዶች ማረፊያ ክፈሎች ሉት ሎጅ ገንብተው አገልግሎት መጀመራቸውን አስረድተዋል። "ይሁንና በአካባቢው የሚገኙ ታሪካዊና ሀይማኖታዊ ቅርሶችን በመጠበቅ ለቱሪዝም ምቹ ለማድረግ ታስቦ በመንግሥት የተገነባው ሙዚዬም ለአንድዓመት ተኩል ያለ ሥራ በመቀመጡ ጎብኚዎች በሚፈለገው መልኩ ወደ አካባቢው አንዳይመጡ አንድ ምክንያት ሆኗል" ብለዋል ። ወደ አካባቢው የሚመጡ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑና የውጭ ጎብኚዎች ደግሞ ፈፅሞ ባለመምጣታቸው ገቢ ማጣታቸውን ተናግረዋል። ሙዚዬሙ ፈጥኖ ወደ ሥራ ባለመግባቱ ለብልሽት መጋለጡንና ቅርሶችም በተገቢው መንገድ ተሰብስበው ባለመቀመጣቸው ለአደጋ የተጋለጡበት ሁኔታ መፈጠሩንም ባለሀብቱ ጠቁመዋል ። ከደብረብርሃን አንኮበር ያለው የአስፋልት መንገድ ግንባታ  መጓተትም  ለአካባቢው ቱሪዝም ዘርፉ ተጨማሪ ማነቆ ሆኗል ይላሉ ኢንጂነር ተረፈ። ሙዚዬሙ ሲገነባ ወደ አካባቢው የሚመጡ የጎብኚዎች ቁጥር እንደሚጨምርና በሚሰጡት አገልግሎትም የተሻለ ገቢ እንደሚያገኙ አስበው እንደነበር የገለፁት ደገሞ በሆቴል አገልግሎት የተሰማሩት አቶ ሲሳይ ጌታቸው ናቸው። "ወደ አካባቢው የሚመጡ የጎብኚዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን ሌሎች ባለሀብቶችም በዘርፉ እንዳይሰማሩ ተጽእኖ ፈጥሯል" ያሉት ባለሀብቱ፣ ሙዚዬሙን ሥራ ለማስጀመር ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ይላሉ ። የአንኮበር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዋሲሁን ብርሃኑ ወረዳው የሥልጣኔና የዘመናዊነት አሻራዎች ያረፉበት ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት መሆኑን ይናገራሉ። "ወረዳው የአንኮበር  ቤተ- መንግሥት መገኛ፣ ጥንታዊት የንግድ መዳረሻና የጉምሩክ ከተማ፣ የፈረሳይ፣የጣሊያንና  የእንግሊዝ መንግሥታት የኤምባሲ አገልግሎትና ሌሎች የዘመናዊ ህንፃ ግንባታ የተጀመሩበት ነው" ብለዋል ። የነገሥታት መገልገያ ቁሳቁስ፣ አልባሳት፣ ጌጣጌጦች እንዲሁም ሃይማኖታዊ  ቅርሶች በወረዳው በስፋት እንደሚገኙ የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው ቅርሶቹን ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ የሙዚዬሙ ግንባታ ቢጀመርም፤በበጀት እጥረት ምክንያት ሥራ ማስጀመር እንዳልተቻለ ገልጸዋል። ለደህንነት ካሜራ መሰል ቁሳቁስ ግዢ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ማስፈልጉን በዋነኝነት ይጠቅሳሉ። በዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶ ባምላክ አስሬ "ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ከአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በተደረገ ውይይት የአንኮበር ሙዚዬምን ሥራ ለማስጀመር በቦርድ እንዲተዳደር ስምምነት ተደርሷል" ብለዋል። የክልሉ ምክር ቤት የቦርድ አባላቱን ሲሰይም ሙዚዬሙ በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ባለው ሃብት ሥራ እንዲጀምርና በቀጣይ ተጨማሪ ሀብት የሚፈለግበትን አቅጣጫ ማስቀመጡን ተናግረዋል። ወረዳዋ  "የዲጅታል የቴክኖሎጂ ሽግግር ለቱሪዝም ልማት”በሚል መሪ ቃል የተከበረውን ዓለም አቀፍ ቱሪዝም ቀን በዞን ደረጃ ባለፈው ወር አክብራለች።                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም