በክልሉ የሴቶችና ህጻናትን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተደረገው ጥረት ውጤት ማስገኘቱን ቢሮው አስታወቀ

87
ሐዋሳ ጥቅምት 17/2011 በደቡብ ክልል ባለፈው በጀት ዓመት የሴቶችና ህጻናትን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተከናወኑ ሥራዎች ውጤታማ እንደነበሩ የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ዛሬ አስታወቀ፡፡ በክልሉ የሴቶች የቁጠባ መጠን ሁለት ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በቢሮው ያለፈው በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2011 ዕቅድ ላይ በሚነጋገረው ጉባዔ ላይ እንደተገለጸው በክልሉ በ2010 በጀት ዓመት የሴቶች ተጠቃሚነት ለማሳደግ በተለያዩ መስኮች የተደረገው እንቅስቃሴ ስኬታማ ነበር። የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን እንዳሉት የክልሉ ሴቶች ያለባቸውን ኢኮኖሚያዊ ችግር ለማቃለልና የውሳኔ ሰጪነት ብቃታቸውን የሚያሳድጉ ተግባራት ተከናውነዋል። በተለይም በግብርና፣ በንግድ በሌሎች ዘርፎች ተደራጅተው የተንቀሳቀሱ ሴቶች ኑሮአቸውን መቀየራቸውን አመልክተዋል፡፡ በተለይ ቁጠባን ማዕከል ባደረጉ የልማት ቡድኖች ተደራጅተው በግብርና ኤክስቴንሽን መርሐ ግብር የተሳተፉ ሴቶች ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡ በሴቶችና በህጻናት ላይ የሚፈጸም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ከመከላከል አንጻር በተለይ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የተገኘው ውጤት በርካታ ህጻናትን  ከመጣል እንደታደጋቸው ተናግረዋል፡፡ በጎልማሶች የትምህርት መርሐ ግብር በማሳተፍ  ዕውቀታቸውን እንዲያሳድጉ መደረጉ ወይዘሮ ሂክማ ገልጸዋል፡፡ የቢሮው ምክትል ኃላፊና የሴቶች ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ አጸደ አይዛ በበኩላቸው እንዳሉት የክልሉ ሴቶች ገቢ በሚያስገኙ ዘርፎች በመሰማራት ካፈሩት ገንዘብ  ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ መቆጠባቸውን ገልጸዋል፡፡ ቁጠባው በአንድ ዓመት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ዕድገት እንደተመዘገበበትም አስረድተዋል። በደቡብ ኦሞ ዞን የበናጸማይ ወረዳ ሴቶችና ህጻናት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አይቶ ገሎ እንዳሉት በወረዳው በተለይ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ያለ ዕድሜ ጋብቻና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የተደረገው እንቅስቃሴ ውጤት አስገኝቷል፡፡ ህጻናት ከፊት ጥርስ ማውጣት ጋር ተያይዞ ''ሚንጊ'' ወይም ገፊ ተብለው ከመጣል እንዲድኑ እስከ ቤተሰብ ድረስ በመውረድ የተከናወነው ሥራ ለውጥ ማስገኘቱን ገልጸዋል፡፡                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም