የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ለረዳት ተማሪ ትራፊክ ፖሊሶች ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ተባለ

1938

አዲስ አበባ ጥቅምት 17/2011 የትራፊክ አደጋን በመቀነስ የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ የረዳት ተማሪ ትራፊክ ፖሊሶች ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ተባለ።

የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ከትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራንና በትምህርት ቤት ካሉ የረዳት ተማሪ ትራፊክ ፖሊሶች ክበብ አስተባባሪ መምህራን ጋር ውይይት አካሂዷል።

በዚህ ጊዜ በኤጀንሲው የመንገድ ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መንግስቱ አድማሱ እንደገለጹት በአዲስ አበባ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በተሰራው ስራ ባለፈው ዓመት የሰው ሞትን በ21 ሰው መቀነስ ተችሏል።

ለዚህም የረዳት የተማሪ ትራፊክ ፖሊስ አስተዋጾኦ የበኩሉን ሚና እንደተጫወተ ጠቅሰው በቀጣይ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ትምህርት ቤቶችና አስተባባሪዎች የበለጠ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የትራፊክ አደጋ የሚያስከትለውን የሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት መውደም፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመቀነስ ረዳት የተማሪ ትራፊክ ፖሊሶቹ ለሁሉም ተደራሽ የሆነ፣ ከወንጀል ነፃና በቀላሉ ማቋረጥ የሚያስችል መንገድ ላይ እንዲያስተናብሩ ለማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ ነው።

በኤጀንሲው የመንገድ ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዘውዱ ወልደዮሐንስ በበኩላቸው በረዳት የተማሪ ትራፊክ ፖሊስ እየመጡ ያሉትን ውጤቶች ለማጎልበት በዘንድሮ ዓመት የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ክበባት አደረጃጀቶች የማጎልበት ስራ ይሰራል።

በዚህም ክበቦቹ፣ ትራፊክ ፖሊሶችና ህብረተሰቡ ተቀራርበውና ተቀናጅተው እንዲሰሩ ይደረጋል ብለዋል።

መምህራን ትውልድን አገር ተረካቢና ጥሩ ዜጋ ለማድረግ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ የትራፊክ አደጋ አስከፊነት፣በሰዎችና በንብረት የሚያስከትላቸውን ችግሮች ማስተማር እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።

ረዳት የተማሪ ትራፊክ ፖሊሶች በተማሪ መውጫና መግቢያ ሰዓት ብቻ ሳይሆን በትምህርት ቤቶቹ አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦችም የድርሻቸውን እንዲወጡ የማድረግ ተግባርም ለመስራት እንደታሰበ አብራርተዋል።

የውይይቱ ተሳታፉዎች በበኩላቸው የትራፊክ አደጋን ለመቀነስና የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ የትምህርት ቤት አመራሮች፣የክበባት አስተባባሪዎችና የትምህርት ቤት ሚኒ ሚዲያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንዲሰሩ ማድረግ ተገቢ ነው ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል።

አቶ ተፈታዊት ገብረእግዚአብሔር በሰጡት አስተያየት የተማሪ ትራፊክ ፖሊሶች ተገቢውን አገልግሎት ለተማሪ ጓደኞቻቸው እንዲሰጡ የሚመለመሉ ተማሪዎችና የክበባት አስተባባሪዎች ፍላጎት ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አቶ ጅብሪል አቡዱልቃደር በበኩላቸው በየመንገዱ የአሸዋ መደፋት፣የመኪና እጥበት፣የጎዳና ንግድ፣ኳስ ጨዋታ፣ ለረዳት ተማሪ ፖሊስ ትራፊኮች ማስተናበር ላይ ችግር እየፈጠረ ስለሆነ መፍትሄ ቢሰጠው ብለዋል።

አቶ አብዲ በላቸው ደግሞ በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚሰሩ ባጃጆች በህጉ መሰረት እንዲሰሩ የሚያደርግ አሰራር መቀየስ ላይ ትኩረት ቢሰጠው ሲሉ አስተያየታቸውን ገልጸዋል።

የትራፊክ አደጋ በዓመት በዓለም ላይ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎችን ለሞትና 50 ሚሊዮን ሰዎችን ለአካል ጉዳት በመዳረግ በገዳይነት በዘጠነኛ ደረጃ ተቀምጧል።