በምዕራብ ሸዋ ዞን ወደ ሥራ ያልገቡ ባለሀብቶች መሬት እንዲመልሱ ተደረገ

74
አምቦ ጥቅምት 17/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን ለኢንቨስትመን ቦታ ተረክበው በውላቸው መሰረት ወደ ሥራ ያልገቡ ባለሀብቶች የተረከቡትን ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንዲመልሱ መደረጉን የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። በጽህፈት ቤቱ የኢንቨስትመት ቅበላና አማራጭ ዕድሎች ጥናት ዋና የሥራ ሂደት መሪ አቶ ባይሳ ቱፋ እንደገለጹት መሬቱ እንዲመለስ የተደረገው በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሦስት ወራት በተካሄደ ክትትልና ግምገማ ነው። መሬቱን እንዲመልሱ የተደረጉት ስምንት የሀገር ውሰጥ ባለሀብቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል ። "ባለሀብቶቹ በዞኑ በጀልዱ፣ ኤጄሬ፣ አደአበርጋና ደንዲ ወረዳዎች ውስጥ ለዘመናዊ ግብርና፣ ለሲሚንቶ ፋብሪካና ለጭማቂ ማቀነባበሪያ ቦታውን ተረክበው ለአምስት አመት ያለስራ አጥረው በማቆየታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል" ብለዋል ። ባለሃብቶቹ ተደጋጋሚ ድጋፍና ክትትል ቢደረግላቸውም ወደ ሥራ መግባት ባለመቻላቸው ቦታው ወደ መሬት ባንክ ገቢ መደረጉን ነው አቶ ባይሳ የገለጹት። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አንዳንድ የጀልዱ ወረዳ ነዋሪዎች በበኩላቸው በወረዳው መሬት የወሰዱ ባለሀብቶች በሚፈለገው ልክ እያለሙ እንዳልሆነ መታዘባቸውንና ዞኑ በባለሀብቶቹ ላይ የወሰደው እርምጃ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል። በዞኑ በኢንቨስትመንት ሥራ የተሰማሩ ባለሀብቶች መብትና ግዴታቸውን በአግባቡ በመወጣት ለዘርፉ እድገትና ለማህበረሰቡ ተጠቃሚነት የበኩላቸውን እንዲወጡ ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል። በምዕራብ ሸዋ ዞን ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 42 ባለሃብቶች በግንባታና በአገልግሎት ላይ መሆናቸው ታውቋል ።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም