የመንግሥታት ግንኙነት(IGR) ፖሊሲ ማዕቀፍ ዝግጅት ተጠናቀቀ

105
አዲስ አበባ ሚያዚያ 22/2010 የመንግሥታት ግንኙነት ፖሊሲ ማዕቀፍ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ። የፌደሬሽን ምክር ቤት 5ኛው የፓርላማ ዘመን ሦስተኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሄዷል። የምክር ቤቱ የዲሞክራሲያዊ አንድነት፣ ሕገ-መንግሥት አስተምህሮና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመንግሥታት ግንኙነት ፖሊሲ (Intergovernmental Relations) ማዕቀፍ የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሪት ፍሬወይኒ ገብረእግዚአብሄር እንደገለጹት፤ ላለፉት አምስት ዓመታት ዝግጅት ሲደረግበት የነበረው የመንግሥታት ግንኙነት ፖሊሲ ማዕቀፍ ዝግጅት ተጠናቋል። የማዕቀፉ ዓላማ የህገ-መንግስቱን ድንጋጌዎች ማስጠበቅ፣ ጠንካራ የህዝቦች ግንኙነት መፍጠር፣ አገራዊና ክልላዊ እቅዶች ሚዛናቸውን ጠብቀው እንዲፈጸሙ ማድረግና በመንግሥታት መካከል ያሉ የጋራ ጉዳዮች በጋራ ለመወሰን መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ ባለፈም በፌደራል መንግሥትና በክልሎች መካከል፣ እንዲሁም በክልሎች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች የሚፈቱበትን የግንኙነት ተቋማዊ ስርዓት መዘርጋትና ማጠናከር ይገኙበታል። ይህንን መነሻ በማድረግ ማዕቀፉን ለማዘጋጀት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ዓብይና የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አብራርተዋል። ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ለመቅሰምም የፌዴራል ስርዓት ከሚከተሉ ደቡብ አፍሪካ፣ ካናዳ፣ ህንድ፣ ስዊዘርላንድና ጀርመን ልምድ መገኘቱን ነው የተናገሩት። በተዘጋጀው ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ግብዓት ለማሰባሰብ ከፌደራልና ክልል ከፍተኛ አመራር አባላት፣ ምሁራን፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሙያና ብዙሃን ማህበራት ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉን አመልክተዋል። ረቂቅ ፖሊሲው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ተቀባይነት ማግኘቱን ሰብሳቢዋ ጠቅሰዋል። እንደ ወይዘሪት ፍሬወይኒ ገለጻ ማዕቀፉ ዘለቄታዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ የህዝብ ጥቅም እንዲከበርና የፖለቲካውን ጤንነት በማስጠበቅ በኩል ትልቅ ሚና ይጫወታል። የምክር ቤቱ አባላት በሰጡት አስተያየት የፖሊሲ ማዕቀፉ በተለይ በክልሎች መካከል ግንኙነቱን የሚያጠናክር ትልቅ መሰረት ነው ብለዋል። ህዝቦችንን በማስተሳሰር ላይ የሚሰሩ ቀጣይ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያደርግ በመሆኑም ማዕቀፉ አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል። ምክር ቤቱ  የማዕቀፉን አስፈላጊነት ካጤነ በኋላም የውሳኔ ሀሳቡን አጽድቆታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም