በምዕራብ ጎንደር ዞን የተረከቡትን መሬት ባላለሙ 237 ባለሃብቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

3703

መተማ ግንቦት 14/2010 በምዕራብ ጎንደር ዞን በግብርና ኢንቨስትመንት ተሰማርተው የተረከቡትን መሬት ባላለሙ 237 ባለሃብቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የኢንቨስትመንት ድጋፍና ክትትል ባለሙያ ወይዘሮ አትጠገብ አስናቀው እንደተናገሩት እርምጃው የተወሰደው ባለሃብቶቹ በውላቸው መሰረት እንዲያለሙ ድጋፍና ክትትል ተደርጎላቸው ባለማሻሻላቸውና ማስጠንቀቂያም ከተሰጣቸው በኋላ ነው ።

እርምጃ ከተወሰደባቸው ባለሃብቶች ውስጥም 23ቱ ውላቸው እንደተቋረጠ ገልጸው “መጠነኛ የአሰራር ችግር ያለባቸው 214 ባለሃብቶች ደግሞ በውላቸው መሰረት ኢንቨስትመንቱን እንዲያከናውኑ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል” ብለዋል

ባለሃብቶቹ ሊነጠቁም ሆነ ማስጠንቀቂያ ሊሰጣቸው የቻለው ከምርት ግምገማ ጀምሮ የተፈጥሮ ሃብትን በመንከባከብና በመጠበቅ እንዲሁም የሰራተኞችን አያያዝ በተመለከተ ደካማ አሰራር በመተግበራቸው እንደሆነ ገልፀዋል።

እንዲሁም በድርጅቶቻቸው ተቋማዊ አደረጃጀት የሌላቸው፣ የልማት አፈፃፀማቸው ዝቅተኛ የሆነ የተሰጣቸውን መሬት ሙሉ በሙሉ ማልማት ያልቻሉና በስነ-ህይወታዊ ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎችን በአግባቡ ያልተወጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ”ባለሃብቶች የእርሻ ኢንቨስትመንቱን ሲያከናውኑ አሰራራቸው ከአካባቢው አርሶ አደር ባልተለየ መልኩ የምርጥ ዘርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ነው” ብለዋል።

በቋራ፣መተማና ምዕራብ አርማጮሆ ወረዳዎች ተሰማርተው ከነበሩት ባለሃብቶች የተወሰደው ከ11 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ወደ መሬት ባንክ የተመለሰ ሲሆን በቀጣይ ተጠንቶ ለተደራጁ ወጣቶች ወይም ለአልሚ ባለሃብቶች እንደሚተላለፍ ገልጸዋል።

ውላቸው ከተቋረጠው ባለሃብቶች መካከል ሊሳ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ተወካይ አቶ ዳዊት ሽፈራው በሰጡት አሰትያየት ”መሬቱን እንድናለማ ቢሰጠንም በተገቢ መንገድ ድጋፍና ክትትል ሳይደረግልን ውላችን መሰረዙ ተገቢ አይደለም” ብለዋል፡፡

በ1997 ዓ.ም በታች አርማጭሆ ወረዳ የተሰጣቸው 3 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያየ ምክንያት ተቀንሶ አንድ ሺህ 196 ሄክታር በውሉ መሠረት ሲያለሙ መቆየታቸውንም ገልፀዋል፡፡

በ2005 በተካሄደ የሽንሸና ስራ ደግሞ  ከዚሁ መሬት ውስጥ 796 ሄክታር የለማ መሬት ተወስዶ ሌላ ያልለማ ተመሳሳይ ሄክታር መሬት እንደተሰጣቸውም አስታውቀዋል፡፡

”ይህን በመሰለ ውስብስብ የአስራር ችግርና የመልካም አስተዳደር እጦት እየተንገላታሁ መቆየቴ እየታወቀ አንድ ጊዜ በተሰጠ ማስጠንቀቂያ ቦታውን መንጠቅ ተገቢ አይደለም” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

በኢንቨስትመንት ስራቸው ከ800 በላይ ጊዜያዊና ከ40 በላይ ቋሚ ሰራተኛ እንደነበራቸውም አቶ ዳዊት ተናግረዋል፡፡

የማስጠንቀቂያ ጽሁፍ ከተሰጣቸው ባለሃብቶች መካከል አቶ ፀሀየ መለስ በበኩላቸው እንደተናገሩት ዝቅተኛ አፈፃፀም ባሳዩባቸው ዘርፎች ጠንክረው በመስራት ራሳቸውንና ሀገራቸውን ለመጥቀም ተዘጋጅተዋል።

ምርታማነትን በማሳደግ የተፈጥሮ ሀብቶችን በመንከባከብና በመጠበቅ እንዲሁም የሰራተኞችን ደህንነትና ጤና በመከታተል ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ በኢንቨስትመንት መሬት ተሰጥቷቸው በማልማት ላይ ያሉ አንድ ሺህ 170 ባለሃብቶች እንዳሉ የተገለፀ ሲሆን በእነዚህ ባለሃብቶች ከ500 ሺህ በላይ ጊዜያዊና ከ11 ሺህ በላይ ቋሚ የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡

ከ126ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በግብርና ኢንቨስትመንት በተሰማሩ ባለሃብቶች እየለማ መሆኑ ከዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።