በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል ጠንካራ ግንኙነት አለ- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

3781

አዲስ አበባ ግንቦት 14/2010 በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል ዘመናት ያለወጡት ጠንካራ ግንኙነት መኖሩን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ይሕን የገለጹት በኬንያ የተለያዩ ዲፕሎማቶች፣ የኬንያ ባለስልጣናትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የግንባት 20 በዓል ሲከበር ነው።

አምባሳደር ዲና እንዳሉት በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል ያለውና ረዥም ጊዜ ያስቆጠረው ግንኙነት በተለያዩ መንግስታት ለውጥም የቀጠለ ነው።

ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ በኢጣልያ ስትወረር ኬንያ ያደረገችውን ድጋፍና ኬንያ የማኦ ማኦ የነፃነት ትግል ወቅት ኢትዮጵያ ለኬንያ ያደረገችውን ድጋፍ ለአብነት አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ ያደረገችው የውጭና አለማቀፍ ግንኙነት ፖሊሲ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ፣ ጣልቃ ገብ ያልሆነና አለማቀፍ ሕጎችን ያከበረ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዛሬ ኢትዮጵያና ኬንያ ላላቸው ጠንካራ ግንኙነት አጼ ኃይለስላሴና ጆሞ ኬንያታ የጣሉት መሰረት ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ መካካለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ እየሰራች ያለች አገር መሆኗንም በመድረኩ ገልጸዋል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም በኬንያ ያደረጉት ጉብኝት የአገራቱን ግንኙነት የበለጠ በማጠናከሩ ረገድ ውጤታማ እንደሆነ ተናግረዋል።

በጉብኝቱ ወቅትም አገራቱ በአቬሽን፣ በመሰረተ ልማት፣ በደህንነት ጉዳዮች ላይ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጠቅሰዋል።

ድንበር ዘለል ሽብርተኝነት፣ ውንብድናና የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ከኢትዮጵያና ኬንያ የጋራ ጉዳዮች መካከል ናቸው ብለዋል፡፡

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሕብረትና ከሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በጋራ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት ጉዳዮች እያደረገች የሚገኘውን አስተዋጽኦ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠው የኬንያ መንግስትም በተመሳሳይ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

በኬንያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ዋና ፀሀፊ ሚስተር መቻሪ ከማሁ ለግንቦት 20 በዓል የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈው የኢትዮጵያና የኬንያ ወዳጅነት ተጠናከሮ ይቀጥላል የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

አገራቱ በፖለቲካ፣ በደህንነት፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሚያደርጉት ትብበር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አክለዋል።

ኬንያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።