የመተከል ዞን ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ መቆራረጥ እንዳማረራቸው ገለጹ፡፡

57
አሶሳ ጥቅምት 16/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአራት ወረዳ ከተሞች ነዋሪዎች በኤሌክትሪክ አገልግሎት እጦት መማረራቸውን ገለጹ፡፡ የክልሉ ኤሌክትሪክ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ችግሩን በአጭር ጊዜ ለመፍታት እየሰራሁ ነው ይላል፡፡ ለወራት የዘለቀ አገልግሎት እጦት እንደገጠማቸው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የገለጹት በዞኑ የደብረዘይት፣ ቡለን፣ ድባጤና ግልገል በለስ ከተሞች ነዋሪዎች ናቸው፡፡ በወምበራ ወረዳ ደብረዘይት ከተማ የ01 ቀበሌ ነዋሪ አቶ እምሩ አራርሳ እንደሚሉት በከተማዋ የኤሌክትሪክ ምሰሶ ከተዘረጋ ከ11 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ ይሁንና ኤሌክትሪክ በከተማው በሳምንት ለአራት ቀናት ያህል ይቋረጣል። በቀሪዎቹ ቀናትም የሚያገኙት ብርሃን ከሻማ ያነሰ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው ገለጻ በርካታ የከተማው ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው በገቢ ማስገኛ ተግባራት ለመሰማራት ቢሞክሩም፤ በተለይ በኤሌክትሪክ ኃይል እጦት የሚከናወኑ ብረታ ብረትና መሰል ሥራዎችን ማንቀሳቀስ አልቻሉም፡፡ የቡለን ከተማ ደግሞ የ24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሰጥ መስመር ከተዘረጋላት አምስት ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ ይሁንና በከተማዋ አገልግሎቱ የሚገኘው በሁለት ወራት አንዴ እንደሆነ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ጸጋነሽ አሰጌ ተናግረዋል፡፡፡ የከተማው ነዋሪዎችና የመንግስት ተቋማትም ላልታቀዱ በጸሐይ ብርሃን ለሚሰሩ ቁሳቁስና ጄኔሬተር እንዲሁም ለነዳጅ ወጪ ተዳርገዋል ብለዋል፡፡ “የአካባቢው መብራት ችግር ከስርጭት ቁጥጥር ማነስ እንጂ። ከመስመር ችግር ጋር የሚገናኝ አይመስለኝም” የሚሉት አስተያየት ሰጨዋ ለዚህ እንደምክንያት የጠቀሱት ደግሞ በከተማው መንግስታዊ ስብሰባ ሲካሄድ መብራት ለቀናት መኖሩንና ስብሰባው ሲያበቃ ደግሞ መብራቱ መቋረጡን ነው፡፡ ችግሩ በተለይ የሴቶችን የስራ ጫና እንዳባባሰው ወይዘሮ ጸጋነሽ ጠቁመዋል፡፡ በድባጤ ከተማ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ገበያው ዓለሙ በተለይም ከነሐሴ 2010 ወዲህ የኤሌክትሪክ ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ አገልግሎታቸው በችግሩ ምክንያት በመዳከሙ የደንበኞቻቸው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰና ግብር ለመክፈል መቸገራቸውን  አስታውቀዋል፡፡ በማንዱራ ወረዳ ውስጥ የምትገኘው ግልገልበለስ ከተማ ነዋሪው አቶ ኡስማን ዳውድ በበኩላቸው ሶስት ወራትን ያስቆጠረው የከተማው የውስጥ ለውስጥ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሳይሰጥ መቀመጡ በምሽት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በስጋት የተሞላ አድርጎታል፡፡ “ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሠራተኞች የህዝብ አገልጋይነት ስሜት ዝቅተኛ ነው ” የሚሉት የወረዳዎቹ ነዋሪዎቹ፣ “ ችግሩ በተለይ የደብረዘይት፣ ቡለንና ድባጤ ከተሞችን እድገት በእጅጉ አዝጋሚ አድርጎታል ” ብለዋል፡፡ የግልገል በለስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ጊሳ ዚሳ የከተማው ኤሌክትሪክ አገልግሎት  የተቋጠው በበጀት እጥረት እንደነበር አመልክተው፣በቅርቡ  ክፍያውን በመፈጸሙ ሥራውን ከሚያከናውነው ድርጅት ጋር አገልግሎቱን ለማስጀመር ስምምነት መደረሱን አስታውቀዋል፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ዋቅጋሪ ረጋሳ በዞኑ ከግልገልበለስ እስከ ደብረዘይት ያለው 170 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት 66 ሺህ ኪሎ ቮልት መስመር ላይ የኃይል መቆራረጥ እንደሚታይ አስረድተዋል፡፡ በተለይም በዞኑ ኤሌክትሪክ አቋርጦ የሚያልፍባቸው የገጠር ቀበሌዎች ላይ የሚገኙ ተክሎች ችግሩን አባብሰዋል ብለዋል፡፡ በቅርቡ ከሁሉም የወረዳ መስተዳድርና ኅብረተሰብ በመተባበር ባህር ዛፍና የተለያዩ ተክሎችን በዘመቻ ለማስወገድ ቢታቀድም ተግባራዊ እንዳልተደረገ ተናግረዋል፡፡ “ስብሰባ ሲኖር መብራት ይኖራ ስብሰባው ሲጠናቀቅ ደግሞ መብራት ይጠፋል ” በሚለው ቅሬታ እንደማይስማሙ የገለጹት ተወካዩ፣ ጽህፈት ቤቱ ይህን መሰል ህገ-ወጥ አሰራር እንደማይከተል አብራርተዋል፡፡ ለጥገናም ሆነ ለሌሎች ጉዳዮች ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ ጽህፈት ቤቱ ለኅብረተሰቡ በግልጽ እንደሚያሳውቅ ጠቅሰዋል፡፡ ሁሉም የጽህፈት ቤቱ ሠራተኞች የአገልጋይት ስሜት የተላበሱ ናቸው የሚል እምነት የለኝም የሚሉት አቶ ዋቅጋሪ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የስነ-ምግባር ትምህርት ሰጥተናል ብለዋል፡፡ ይሁንና ሠራተኞች የተሰጣቸውን ትምህርት ተግባራዊ ስለማድረጋቸው ግን ክትትል አልተደረገም ይላሉ፡፡ አሁን በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን ለመቀላጠፍ በሚደረገው ጥረት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን አቶ ዋቅጋሪ አስረድተዋል፡፡ ጽህፈት ቤቱ በሐምሌ 2010 መደራጀቱን ያስታወሱት ተወካዩ፣በመተከል፣ አሶሳ ና ካማሽ ዞኖች ተሸከርካሪዎችና ባለሙያዎች ያሉት የጥገና ቡድን እየተደራጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለዓመታት የዘለቀውን የነዋሪዎችን ቅሬታ በአንድ ወር ውስጥ ለማቃለል ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ በደብረዘይት፣በቡለን፣ በድባጤና በግልገልበለስ ከተሞች 70 ሺህ የሚጠጋ ህዝብ እንደሚኖር መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም