አትሌት ሰለሞን ባረጋ የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአምስት ሺህ ሜትር ክብረ-ወሰን ባለቤት ሆነ

415

አዲስ አበባ ጥቅምት 16/2011 ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰለሞን ባረጋ የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአምስት ሺህ ሜትር ርቀት የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት ሆነ።

የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ዕውቅና በሰጣቸው ውድድሮች ላይ በተለያዩ ርቀቶች የተመዘገቡ የዓለም ክብረ-ወሰኖችን በማጣራት ዛሬ በሰባት የውድድር አይነቶች የተመዘገቡ የዓለም ክብረ-ወሰኖችን አጽድቆ ይፋ አድርጓል።

በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰለሞን ባረጋ በነሐሴ 2010 ዓ.ም በቤልጂየም ርዕሰ-መዲና ብራሰልስ ባደረገው የአምስት ሺህ ሜትር ውድድር 12 ደቂቃ ከ43 ሰከንድ ከሁለት ማይክሮ ሰከንድ የገባበት ጊዜ የዓለም ከ20 ዓመት በታች ክብረ-ወሰን እንዲሆን ተወስኗል።

ከዚህ በፊት ክብረ-ወሰኑ ተይዞ የነበረው በኢትዮጵያዊ አትሌት ሐጎስ ገብረህይወት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2012 በፈረንሳይ ፓሪስ በተደረገ ውድድር ሲሆን የገባበት ሰዓት 12 ደቂቃ ከ47 ሰከንድ ከ53 ማይክሮ ሰከንድ ነበር።

አትሌት ሰለሞን ባረጋ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ውድድሮች ስኬታማ ጊዜ በማሳለፍ ላይ ይገኛል።

የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ኬንያዊው አትሌት ኤሊውድ ኪፕቾጌ በበርሊን ማራቶን በወንዶች ውድድር ሁለት ሰዓት ከአንድ ደቂቃ ከ39 ሰከንድ የገባበት ጊዜ የዓለም ክብረ ወሰን እንዲሆን ወስኗል።

ክብረ ወሰኑ ከዚህ በፊት ተይዞ የነበረው በሌላኛው ኬንያዊ ዴኒስ ኪሚቶ ሲሆን አትሌቱ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2014 በበርሊን ማራቶን ሁለት ሰዓት ከሁለት ደቂቃ ከ57 ሰከንድ ያስመዘገበው ሰዓት በርቀቱ የዓለም ከብረ-ወሰን ሆኖ ቆይቷል።

ከአትሌት ሰለሞን ባረጋ ክብረ-ወሰን በተጨማሪ ስድስት የዓለም ክብረ-ወሰኖችን አጣርቶ አጽድቋል።

በዚሁ መሰረት የዓለም ከ20 ዓመት በታች የ110 ሜትር ወንዶች መሰናክልና አራት በ100 ሜትር (4x100m)፣ በቤት ውስጥ ውድድር የወንዶችና ሴቶች አራት በ800 እና በዘጠኝ የስፖርት አይነት ውድድሮች(ዴክታትሎን) ወንዶች ተይዘው የነበሩ የዓለም ክብረ-ወሰኖች ለሌሎች ተወዳዳሪዎች ተሰጥቷል።

ዕውቅናና ፈቃድ በተሰጣቸው ውድድሮች ላይ ማሸነፍ፣ የውድድር ሜዳዎቹ የሚፈለገውን መስፈርት ያሟሉ መሆንና አትሌቶች በአበረታች ቅመም ምርምራ ውጤት ጤነኛ መሆናቸው መረጋገጥ አትሌቶች የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት የሚሆኑባቸው ዋነኛ ቅደመ-ሁኔታዎች ናቸው።