በአፍሪካ ሰላምን ለማጎልበት የመምህራን ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ሰላምን ለማጎልበት የመምህራን ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ ግንቦት 14/2010 በአፍሪካ ሰላምን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት መምህራን የሚጫወቱት ሚና ወሳኝ መሆኑን በአፍሪካ ህብረት የትምህርት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢያትሪክ ኒጂንጋ ገለፁ። "በአፍሪካ ቀንድና አካባቢው አገራት መምህራን ስልጠናና ልማት ለሰላም ግንባታ" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ የተዘጋጀው የሁለት ቀናት አውደ ጥናት ዛሬ ተጀምሯል። በአውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ ኃላፊዋ ዶክተር ቢያትሪክ ኒጂንጋ ባደረጉት ንግግር ትምህርት በሰላም የታነፀ ዜጋን ለመፍጠርና ከሁከት የፀዳ አስተሳሰብን ለማጎልበት ቁልፍ ሚና እንዳለው ጠቅሰው በዚህ ረገድ የመምህራን ድርሻ ወሳኝ ነው ብለዋል። "በአፍሪካ የሚታለመውን የጋራ ኃላፊነት፣ አንድነት እንዲሁም ነጻነቱን የተጎናፀፈና ሰፊ አድማስ ያለውን ውህደት እውን ማድረግ የሚቻለው በሰላምና በትምህርት መካከል ያለውን ቁርኝት በማጠናከር ብቻ ነው፤" ሲሉ ኃላፊዋ ገልፀዋል። የአፍሪካ አህጉራዊ የትምህርት ስትራቴጂ ሰላማዊ የትምህርት ሂደትን የሚሰብክ ከመሆኑም በላይ ቀውሶች በሚፈጠሩበት ወቅት እንኳ የመማርና ማስተማር ሂደቶች እንዳይስተጓጎሉ ጥበቃና ዋስትና እንዲሰጥ ትኩረት ያደርጋል ሲሉም ተናግረዋል። በመሆኑም መምህራን ለሰላም ዋጋ የሚሰጥ፤ ግጭትን የሚጠላ አእምሮን ያጎለበተና ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋን በመፍጠር ረገድ የሚጫወቱት ሚና ቁልፍ መሆኑንም ዶክተር ኒጂንጋ ገልፀዋል። መምህራን በሚሰጧቸው ሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ውስጥ የሰላምን ዋጋ ማካተት የሚያስችላቸውን አቅም ለማሳደግ አስፈላጊውን ስልት መቀየስ ከአፍሪካ አገራት እንደሚጠበቅም ኃላፊዋ አሳስበዋል። አክለውም ትምህርት በሰላም ግንባታ ሂደት ትልቅ ድርሻ ያለው በመሆኑ መምህራን የወጣቶችን አስተሳሰብ ለመቀየር ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል። ለመምህራኑ የሚሰጠው ስልጠናም በሰላም የትምህርት አሰጣጥ ስልት አማካኝነት ውይይትን መሰረት ባደረገ የግጭት መከላከልና መፍትሄ ማፈላለግ እንዲሁም ሰላማዊ ባህልንና የመቻቻል አስተሳሰብን በአፍሪካ ህፃናትና ወጣቶች አእምሮ እንዲበለፅግ ያለመ መሆን ይኖርበታል ሲሉም አስገንዝበዋል። በአፍሪካ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የህዝብ ቁጥር ከ35 ዓመት በታች የዕድሜ ክልል ነው ያሉት ኃላፊዋ ይህም ለአፍሪካ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና ፖለቲካ ዕድገት ልዩ ዕድል መሆኑን ጠቅሰዋል። በአውደ ጥናቱ ላይ የአፍሪካ አገራት የትምህርት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተወካዮች፣ የአፍሪካ ህብረት የትምህርት ዘርፍ እና የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የባህልና ሳይንስ ድርጅት (ዩኔስኮ) ተወካዮች ተካፍለዋል።