የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በግብርና ምርት እሴት በሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት አድርጓል

142
አዲስ አበባ ጥቅምት 15/2011 የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በግብርና ምርቶች ላይ እሴት የሚጨምሩና የማምረቻ ዘርፉ ሊደግፉ የሚችሉ የፈጠራና ቴክኖሎጂ ውጤቶች በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴር በግብርና፣ በግብር አሰባሰብ፣ በጤናና ሌሎች ዘርፎች ውጤታማና ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ምርምር ውጤቶች እንዲመረቱና ምርቶቹም ተግባራዊ እንዲሆኑ በሚገባ አልሰራም። ከ14 ዓመታት በፊት ጀምሮ በአገሪቱ እየተተገበረ ያለው የ70/30 ትምህርት ፖሊሲ የራሱ ድክመት ቢኖረውም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ግን የተማረ የሰው ኃይል እንዲፈጠር አድርጓል። በአገሪቱ ሰፊ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ለማፍራት፤ ስራ መፍጠር የሚያስችል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ንድፈ ሃሳብና ክህሎት ያላቸው ምሩቃን እንደሚያስፈልጉ ገልጸው፤ በዚህ ዘርፍ ምሩቃኑ እንዲፈጠሩ የትምህርት ፖሊሲው አወንታዊ ሚና እንደነበረው ያምናሉ። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙና ተመርቀው የወጡ ወጣቶች የማምረቻውን ዘርፍ ሊደግፉ የሚችሉ ለአገር እድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው የቴክኖሎጂ አነስተኛና ጥቃቅን ድርጅቶች መፈጠራቸውንና የፈጠራ ምርቶች ተግባራዊ መደረጋቸውን ገልጸዋል። በተለይም በምህንድስና ትምህርት መስኮች የተመረቁ ወጣቶች የፈተና ማረሚያ፣ የሆፒታሎች ዲጂታል ፕላትፎርም፣ ሰው አልባ አውሮፕላንና እውነተኛ የትምህርት ማስረጃ ማረጋጋጫ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠራቸውን ለአብነት አንስተዋል። በሳይንስ፣ ፈጠራና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ሙከራዎቹ አበረታች እንደሆኑ የሚናገሩት ሚኒስትሩ፣ ወጣቶችን የማገዝና ድጋፍ የማድረግ ስራ እንዳልተሰራ አብራርተዋል።  የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ በሚል መጠሪያ በአዲስ የተዋቀረው ሚኒስቴር አገራዊ አኮኖሚውን በተለይም በግብርና ምርቶች ላይ እሴት የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎች እንዲወጡ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። ነገር ግን ግብርናው ምን ያህል የተትረፈረፈ ምርት ቢያመርትም ከአገልግሎት ዘርፉ ጋር ካልተሳሰሩ ለአገር ምጣኔ ሀብታዊ እድገት እምርታ እንደማያመጣ ገልጸው፤ የግብርና ምርቶችን ከአገልግሎቱ ጋር ማስተሳሰር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። እውቀት እንጂ ብዙ ኢንቨትመንት የማይጠይቁ የሶፍትዌር ፈጠራዎች እንዲጎለብቱና ንግድና አገልግሎትን በቴክኖሎጂ እንዲተሳሰሩ ማድረግ የሚኒስቴሩ የትኩረት አቅጣጫ እንደሚሆን አመልክተዋል። በሌላ በኩል ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሚደረገው መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር የማምረቻው ዘርፍን ማሳደግ እንደሚያስገድድ ገልጸዋል። ''የማኑፋቸሪንግ ዘርፉ ግን እያደገ ቢመጣም ድርሻው ግን 6 በመቶ ብቻ ነው'' ብለዋል። በርካታ አገሮች ወደ መካከለኛ ገቢ ሲሸጋገሩ የማምረቻው ዘርፍ ብቻውን ከ20 በመቶ በላይ ድርሻ እንደሚኖረው በመጥቀስ በፍጥነት ለማደግ ማኑፋቸሪጉን የሚደግፉ ስራዎች ላይ በስፋት መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የተሽከርካሪ መለዋወጫዎች በሙሉ ከውጭ ይመጣሉ፣ በርካታ ኢንዱስትሪዎችም መለዋወጫ በማጣት እንቅስቃሴ አቁመዋል የሚሉት ዶክተር ጌታሁን፣ ከውጭ የሚገቡ የመኪና፣ ባቡርና የኢንዱስትሪ መለዋወጫዎች እንዲፈጠሩ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። ስለሆነም በምርምር ተቋማትና በዩኒቨርሲቲዎች በንድፍ ደረጃ ያሉ ቴክኖሎጂዎች ወደ ምርት የሚቀየሩበት የቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ተቋማት እንዲፈጠሩ ማድረግ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም