የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ሴት ፕሬዚዳንት በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እይታ

116
የካቢኔ የሃላፊነት ቦታን የ50 በመቶ ድርሻ በሴቶች በመሙላት ታሪክ የፃፈችው ሃገር ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ደግሞ ሴት ፕሬዚዳንትን ወደ ሃላፊነት በማምጣት አለምን እያስገረመች ትገኛለች። ጉዳዩም ዕውቅ የሚባሉ ግዙፍ የአለማችን የሚዲያ ተቋማትን ቀልብም ስቧል፤ እየሳበም ይገኛል። በአራቱም ማዕዘናት የሚገኙ አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ ወደ ሃላፊነት ያመጣችውን ሴት ፕሬዚዳንት ዋቢ ያደረጉ ዘገባዎቻቸውን ይዘው ወጥተዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም። የኢትዮጵያው ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ የስልጣን መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለፓርላማ አቀረቡ በማለት ኢዜአን ዋቢ በማድረግ የቅድሚያ ዘገባውን ይዞ የወጣው ሲ ኤን ኤን የ63 አመቱ ሰው እኤአ በ2013 ወደ ሃላፊነት መምጣታቸውን ጠቅሷል። ሲኤን ኤን ዘገባውን ሲቀጥልም ዶ/ር ሙላቱ ወደ ፕሬዚዳንትነት ከመምጣታቸው በፊት በተለያዩ ሃላፊነቶች እንዲሁም በጃፓን እና አዘርባጃን በዲፕሎማሲው ዘርፍ ሃገራቸውን ሲያገለግሉ እንደቆዩም አስታውሷል። ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ ምክር ቤትን ሙሉ ይሁንታ በማግኘት ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊት በቱርክ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር በመሆን ሲያገለግሉ እንደነበርም አክሏል። ልክ እንደ ሲኤን ኤን ሁሉ ሌሎች አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም ኢዜአን በዋና የዜና ምንጭነት በመጥቀስ ፕሬዚዳንቱ የስልጣን መልቀቂያ ማቅረባቸውን ሲዘግቡ በተለይ የምዕራብ አፍሪካዎቹ ዘ ፐንች እና ቫንጋርድ ለጉዳዩ ሰፋ ያለ የዘገባ ሽፋን ሰጥተውታል። በሌላም በኩል የተጠቀሱት አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ሌሎች ደግሞ ፕሬዚዳንቱን የተኳቸውን ሴት ፕሬዚዳንት አስመልክተው ዘርዘር ያለ መረጃዎቻቸውን እያሰራጩ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ የመጀመሪያ የሆነችውን ሴት ፕሬዚዳንት ወደ ሃላፊነት ማምጣቷን የፃፈው ዋሺንግተን ፖስት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በልምድ የካበቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዲፕሎማት መሆናቸውንም መስክሯል። የወንዶች የበላይነት በሚስተዋልበት የሃገሪቱ ባህል፤ የሴቶች የሃገር መሪነት የማህበረሰቡን ህይወት ለመቀየር ሴቶች የሚኖራቸውን ውሳኔ ሰጪነት እንዲለመድ ያደርጋል በሚል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ፍፁም አረጋ በትዊተር ገፃቸው ላይ ያስቀመጡትን ሃሳብ አጋርቷል። የፕሬዚዳንቷ ሃላፊነት እንዲሁም ባለፈው ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ግማሹን የካቢኔ ሃላፊነት የወሰዱት ሴቶች በአፍሪካ በህዝብ ብዛቷ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ለምትገኘው ሃገር ትዕምርታዊ ሊሆን እንደሚችል ዋሺንግተን ፖስት በዘገባው አሳይቷል። ኢትዮዽያ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ብቸኛ የሆኑትን ሴት ፕሬዚዳንት አስመረጠች ሲል የዘገበው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የ68 አመቷ ሳህለወርቅ ዘውዴ በትናንትናው ዕለት የስራ መልቀቂያ ያስገቡትን ሙላቱ ተሾመን እንደሚተኩም አስነብቧል። ሃገሪቷ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚኒስትር ሃላፊነትን ለሴቶች የሰጠችበትን ሁኔታ ያስታወሰው ኤ ኤፍ ፒ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ከዚህ ቀደም ያልነበረው የሰላም ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ ኢንጂነር አይሻ ሞሃመድን ደግሞ በአፍሪካ የመጀመሪያዋ የመከላከያ ሚኒስትር ሃላፊ እንዲሆኑ ማድረጓን ፅፏል። ከቅርብ አመታት በፊት በአፍሪካ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ሴት ፕሬዚዳንቶች እንደነበሩ የዘገበው የመረጃ ምንጩ እኤአ ከ2006 እስከ 2018 ላይቤሪያን የመሩትን ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍን እና እኤአ ከ2012 እስከ 2014 የማላዊ ፕሬዚዳንት የነበሩትን ጆይሴ ባንዳን አስታውሷል። ኤ ኤፍ ፒ አዲሷ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአፍሪካ በስራ ላይ ያሉ ብቸኛዋ ሴት ፕሬዚዳንት እንደሆኑም አስቀምጧል። የኢትዮጵያ ፓርላማ ሳህለወርቅ ዘውዴን የመጀመሪያዋ የሀገሪቱ ሴት ፕሬዚዳን አድርጎ መምረጡን የዘገበው ዘኔሽን፤ ግለሰቧ ወደ ፕሬዚዳንትነቱ ከመምጣታቸው በፊት በመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካ ህብረት ተጠሪ ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ፅፏል። የብሪታኒያው የዜና ወኪል ቢቢሲ በበኩሉ ሳህለወርቅ ዘውዴ የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ሆነች በማለት ዘግቧል። ፕሬዚዳንቷ በመንግስታቱ ድርጅት ውስጥ በሃላፊነት ሲሰሩ የቆዩ አንጋፋ ዲፕሎማት መሆናቸውን ያከለው ቢቢሲ በሃላፊነት መቀበያ ንግግራቸው ስለ ሰላም አስፈላጊነት አፅንኦት ሰጥተው መናገራቸውን ጠቁሟል። ፕሬዚዳንቷ ሃገራቸውን በመወከል በፈረንሳይና ጂቡቲ በከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራዎች ላይ አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውን ያስታወሰው ሲኤን ኤን እስካለፈው ሰኔም በመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ሲሰሩ እንደነበር ዘግቧል። የሬውተርስ የዜና ወኪል ደግሞ በኢትዮዽያ ፓርላማ ሙሉ ይሁንታን ያገኙት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን በመተካት የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት መሆናቸውን የዘገበ ሲሆን ሲቢሲ ኒውስ በበኩሉ ፕሬዚዳንቷ በተለያዩ የተባበሩት መንግስታት ቢሮዎች ውስጥ በዘርፈ ብዙ ሃላፊነቶች ላይ ሰርተዋል ብሏል። መገናኛ ብዙሃኑ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በፕሬዚዳንትነት ከተመረጡበት ቅፅበት አንስቶም ሆነ ከመመረጣቸው በፊት በርካታ መረጃዎችን ይዘው ወጥተዋል፤ መረጃውን በተለያዩ የመረጃ ማስተላለፊያ አግባቦችም እየተቀባበሉት ይገኛሉ። (ኢዜአ ሞኒተሪንግ)
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም