ዜጎች ደም በመለገስ ችግር ወስጥ የወደቁ ወገኖችን ሕይወት እንዲያተርፉ ሚኒስትሩ ጠየቁ

1150

መቀሌ ጥቅምት 15/2011 ዜጎች ደም በመለገስ ችግር ወስጥ የወደቁ ወገኖችን ሕይወት እንዲያተርፉ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር አሚር አሚን ዛሬ ጠየቁ።

ሚኒስትሩ በመቀሌ ከተማ ደም ለግሰዋል።

ዶክተር አሚር በከተማው እየተካሄደ ካለው 20ኛው አገር አቀፍ የጤና ልማት ጉባዔ  በተጓዳኝ ደም ለግሰዋል፡፡ በዚሁ ወቅት  እንዳስገነዘቡት ዜጎች በደም እጥረት የሚቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት ደም ልገሳ መለገስ ይጠበቅባቸዋል።

በርካታ ዜጎች በደም እጥረት ምክንያት የቀዶ ጥገና ህክምና እንዲራዘም ከማድረግ ባለፈ ውድ ህይወታቸውን እያጡ ያሉት ማጣታቸውንመር አስረድተዋል፡፡

በአገሪቱ ደም ልገሳ ባህል እንዲሆን በየደረጃው የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች የማያቋርጥ ቅስቀሳና የግንዛቤ ማሳደጊያ ትምህርት መስጠት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ዶክተር አሚር።

በኢትዮጵያ ለ70 ጊዜ ደም በመለገስ የሚታወቁትና የብሄራዊ ደም ባንክ የቅስቀሳ ክፍል አባል ሲስተር አሰጋች ጎሳ ሰብዓዊነት ከሚገለፅባቸው በጎ ተግባራት መካከል አንዱና ዋናው ደም ለተቸገረ ዜጋ መስጠት መሆኑን ገልጸዋል።

”ለእያንዳንዱ ዜጋ ደም መለገስ አንድ ጠብታ ነው።የደም እጥረት ላጋጠመው ግን ዘለዓለማዊ ህይወት ማስቀጠል መሆኑ ሳንዘነጋ ደም መለገስ ይገባናል” ብለዋል።

ለጉባዔው ከአዲስ አበባ የመጡት ወይዘሮ ሙሉ ወንድራድ ለ49ኛ ጊዜ ደም መለገሳቸውን ይናገራሉ።

”በትክክል ለሚገነዘበው ሰው ደም መስጠት ጤና ነው።ደም መስጠት የህሊና እርካታ ነው።ስለዚህ በየአካባቢው በሚገኙ የደም ባንኮች በመሄድ ደም መስጠት አለብን” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የመቀሌ የደም ባንክ ማዕከል ባለሙያ አቶ መኮንን አስፍሃ የጉባዔው ተሳታፊዎች እስከ እኩለ ቀን ድረስ ሚኒስትሩን ጨምሮ 26 የሚሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችና ባለሙያዎች ደም መለገሳቸውን አስታውቀዋል።

ማእከሉ በተያዘው በጀት ዓመት ከ13ሺህ የደም ከረጢት በላይ ለመሰብሰብ እቅድ የያዘ ሲሆን፣እስካሁን ከሁለት ሺህ በላይ የደም ከረጢት መሰብሰቡን ገልጸዋል።