ዩኒቨርሲቲው በኦሮሚያ ክልል ስምንት ወረዳዎች ከአርሶ አደሮች ጋር በመቀናጀት የአዝዕርት ዝርያዎችን እያሰራጨ ነው

58
ሐረር ጥቅምት 15/2011 የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በኦሮሚያ ክልል ስምንት ወረዳዎች ከሚገኙ አርሶ አደሮች ጋር በመቀናጀት 78 ምርጥ የአዝዕርት ዝርያዎችን አባዝቶ እያሰራጨ መሆኑን ገለጸ። በዞኖቹ በማህበራት የተደራጁ አርሶ አደሮች ከዩኒቨርሲቲው ተቀናጅተው በሚያከናውኑት ቴክኖሎጂ ተኮር የምርጥ ዘር ብዜት ውጤታማ ሆነናል ይላሉ። የዩኒቨርሲቲው የተቀናጀ የዘር ዘርፍ ልማት ፕሮጀክትሥራ አስኪያጅ አቶ ደንደና ገልሜሳ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስረዱት ዩኒቨርሲቲው በምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ ዞኖች በተመረጡ 3 ሺህ አርሶ አደሮች ጋር ከምርምር ተቋማት የተገኙ ምርታማና በሽታ ተቋቋሚ ምርጥ ዝርያዎችን በማባዛት ተጠቃሚ እያደረጋቸው ነው። ከመካከላቸውም 1ሺ 200 ሴት አርሶ አደሮች ናቸው። በስምንት ወረዳዎች  በሚገኙ 38 የገጠር ቀበሌዎች እየተከናወነ ባለው ሥራ በ23 ማህበራት  የተደራጁ አርሶ አደሮቹ  ለአካባቢያቸው ተስማሚነት ያላቸውን በዋነኝነት የስንዴ፣የበቆሎ፣የማሽላና የቦሎቄ ዝርያዎች መረጣና ብዜት ላይ መሰማራታቸውን አስታውቀዋል። ባለፉት ጊዜያት ምርጥ ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ የሚሰራጩት ያለ ምንም ሙከራ ነበር ያሉት አቶ ደንደና፣የአሁኑ ሙከራ ግን አርሶ አደሩ በማሳው ላይ ሰብሉን አብቅሎ ውጤቱን ከተመለከተ በኋላ የሚስማማውን ዝርያ የሚመርጥበት በመሆኑ ልዩነት እንዳለው ገልጸዋል። በመሆኑም በዞኖቹ የሚገኙ ዘር አቅራቢ ዩኒየኖችና ማህበራት፣ የምርጥ ዘር አቅራቢ ድርጅቶች፣ የግብርና ቢሮዎችና ባለሙያዎች ከዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎችና ልምድ እንዲቀስሙ እየተደረገ ነው ብለዋል። በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የኩርፋ ጨሌ ወረዳ የግብርና ባለሙያ አቶ ግዛው ልኬለው ዩኒቨርሲቲው በወረዳው ህዳሴ፣ኪንግ በርድና ኦበራ የተባሉ የስንዴና እንዲሁም የአፕል ዝርያዎችን ከአርሶ አደሩና ከግብርና ባለሙያዎች ጋር መምረጡ ይናገራሉ። ከሰብል ዝርያዎቹ ''ህዳሴ'' የተባለውን ዝርያ የዝናብ እጥረትንና በሽታን ተቋቁሞ ምርት በመስጠት የተሻለ ሆኖ እንዳገኙትና ከደቡብ ክልል የመጣው የአፕል ዝርያ ለ16 አርሶ አደሮች ተሰጥቶ ሙከራ እየተደረገበት መሆኑን ጠቁመው፣ሥራው አርሶ አደሩን ስለሚያነሳሳ መበረታታት አለበት ብለዋል። ''ዩኒቨርሲቲው በተለይ ከሴት አርሶ አደሮች ጋር በሚሰራው ተግባር ተኮር የዘር መረጣ ሴቶች ተጠቃሚ ሆኗል። በአንድ ዓመትም 25 ኩንታል ምርጥ የስንዴ ዘር በማምረት ለአካባቢው አርሶ አደሮች አንዱን ኩንታል በ4 ሺህ ብር ሽጠናል'' '' በማለት አስተያየታቸውን የሰጡት በሜታ ወረዳ ዱርሲቱ ቢሊሱማ ቀበሌ በዘር ብዜት ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱት ሴት አርሶ አደር ሚስራ አደም ናቸው። በቀርሳ ወረዳ ወተር ቀበሌ  በዚሁ ሥራ የተሰማራው አርሶ አደር ሸረፍ ኡመሬ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ቦሎቄ፣ስንዴ፣ድንችና ሌሎች ምርጥ የሰብል ዝርያዎችን በተግባር ተኮር ቴክኖሎጂ ታግዘው በማምረትና ለአካባቢያቸው ተስማሚ የሆኑትን ዝርያዎች ለሌሎች አርሶ አደሮች እያሰራጩ መሆኑን ተናግረዋል። ቀደም ሲል ይጠቀሙባቸው የነበሩት የድንችና ስንዴ ዝርያዎች በክረምት ወቅት ብቻ የሚበቅሉና በሽታን የመቋቋም አቅማቸው ደካማ እንደነበር ያስታወሱት አርሶ አደር ሸረፍ፣በምርምር የተገኙት ዝርያዎች በሽታን በመቋቋምና በተሻለ ምርት ሰጪነታቸው ተመራጭ መሆናቸውን  አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሁለተኛ አንጋፋው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ በጀት ዓመት በ154 ፕሮጀክቶች ላይ ምርምር  እያከናወነ ይገኛል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም