የመማሪያ ክፍልና የመጽሐፍት እጥረት በትምህርታቸው ላይ እንቅፋት እንደሆነባቸው ተማሪዎች ተናገሩ

88
ጥቅምት 15/2011 በአዲስ አበባ ከተማ በኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት በሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች የትራንስፖርት፣  የመማሪያ መጽሐፍትና  የክፍል እጥረት እንደገጠማቸው  አስተያየታቸውን የሰጡ ተማሪዎችና መምህራን ተናግረዋል። አፋቸውን በፈቱበት በኦሮምኛ ቋንቋ መማራቸው ትምህርታቸውን በቀላሉ ለመረዳት እንደሚያስችላቸው በጀኔራል ታደሰ ብሩ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሲፈን አሸናፊና የጋራ ጉሪ ትምህርት ቤት ተማሪው ረቡ አብዲ ገልጸዋል። አፉን በፈታበት ቋንቋ መማር በመጀመሩ ደስተኛ መሆኑን የገለፀው ተማሪ ባይሳ ተሻለ በበኩሉ እስካሁን የመማሪያ መጽሐፍት አለመሰጠቱ በትምህርቱ ላይ ጫና እንደፈጠረበት ገልፆ አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጥ እንደሚገባም ነው የተናገረው። የትምህርት ቤቶቹን የመጻህፍት እጥረት ለመቅረፍ በህትመት ላይ መሆኑን የገለፁት የከተማዋ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ታከለ ከበደ በቅርቡ 50 ሺህ መጻህፍት ታትመው ለተማሪዎች እንዲደርሳቸው ይደረጋልም ነው ያሉት። የጄነራል ታደሰ ብሩ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ዳባ ተረፈ  እንደሚሉት የተማሪዎች ቁጥር ከአምናው በእጥፍ ጨምሮ ዘንድሮ 4 ሺህ 600 በመድረሱ የክፍል እጥረት አጋጥሟቸው ከክፍለ ከተማና ከከተማ አመራሮች ጋር በመነጋገር ተጨማሪ ሶስት ግቢዎችን በማመቻቸት ትምህርት እንዳይስተጓጎል ተደርጓል። የጋራ ጉሪ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የወላጅ ኮሚቴ አቶ ደሜ አበራ በትምህርት ቤቱ የተቀናጀ መማር ማስተማር እንደሌለ ይናገራሉ። በትምህርት ቤቱ የመማሪያ ክፍሎች እጥረት በመኖሩ ምክንያት ተማሪዎች በፈረቃ ለመማር እንደተደረገና የትራንስፖርት ችግር መኖሩንም ነው አቶ ደሜ ያነሱት። የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር ሙለታ ያደታ ችግሩ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ለየካ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረባቸውን አንስተዋል። የየካ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዮት ድንቁ በበኩላቸው  የክፍል እጥረቱን ለመፍታት የሚያስችል ቤት ለመከራየት የጨረታ ሂደት ላይ ነን ብለዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም በቀጣይ ዓመት ህንጻ ለማስጀመር የካርታና የባለቤትነት ሰነዶች እንዲሰጣቸው  በሂደት ላይ እንደሚገኙ  የተናገሩት አቶ አብዮት  እስከ መጪው ጥር ወር ተማሪዎች በፈረቃ እንዲማሩ ጊዜያዊ መፍትሄ መቀመጡንም  ጠቁመዋል። የትራንስፖርት ችግሩን ለመፍታት ተማሪዎችን የማጓጓዝ አገልግሎት ከሚሰጡ አካላት ጋር ፈረቃን ታሳቢ ያደረገ አዲስ ውል እንደሚፈራረሙ ነው አቶ አብዮት የጠቆሙት። የከተማዋ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ታከለ ከበደ ዘንድሮ ሁሉም የመንግስት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር የሚፈልጉ ኦሮምኛ ተናጋሪ ተማሪዎችን እንዲያስተናግዱ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱንም ነው የገለጹት። በአማርኛ እና በኦሮምኛ ጎን ለጎን መማራቸው የባህል ትውውቅ፣ የቋንቋ መላመድና የማህበራዊ ትስስራቸውን እንደሚያጠናክረው ታምኖበትም  ነው የተጀመረው ብለዋል። በዚህም ዘንድሮ በጀመሩት ቀርሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 700 ተማሪዎች፣ በጨፌ ቡልቡላ ትምህርት ቤት 1 ሺህ 100 ተማሪዎች፣ በየካ ቦሌ ትምህርት ቤት 300 ተማሪዎች በኦሮምኛ እየተማሩ ነው ብለዋል። የኦሮሚያ ክልል ለቢሮው ባስረከባቸው አራት ትምህርት ቤቶችና ዘንድሮ በመጀሩት በሶስቱ ትምህርት ቤቶች 600 መምህራን ተመድበው በኦሮምኛ ቋንቋ እያስተማሩ መሆኑን ጠቁመዋል። በአዲስ አበባ በሰባት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ12 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በኦሮምኛ ቋንቋ እየተከታተሉ መሆኑን ዶክተር ታከለ ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም