ሦስተኛው ዙር የምግብ ዋስትና ፕሮግራም የቤት ለቤት ምዝገባ በማካሄድ ከነገ በስትያ ይጀመራል

65
አዲስ አበባ ጥቅምት 14/2011 በአዲስ አበባ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የኀብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ሦስተኛው ዙር የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ከነገ በስትያ የቤት ለቤት ምዝገባ በማካሄድ እንደሚጀመር የመዲናዋ የጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ አስታወቀ፡፡ የቢሮው ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው ዛሬ በሰጡት መግለጫ በሦስተኛው ዙር የምግብ ዋስትና ፕሮግራም በቀሪ 26 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ የደሃ ደሃ ነዋሪዎች ምዝገባ ይካሄዳል። በምዝገባው ከ92 ሺህ በላይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኀብረተሰብ ክፍሎች በማህበረሰብ አቀፍ ስራዎችና በቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል። የቤት ለቤት ምዝገባ ፕሮግራሙን ለማስጀመር በ26 ወረዳዎች ያሉ 58 ሺህ የኀብረተሰብ ክፍሎችን በፕሮግራሙ ዙሪያ በማወያየት ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች መከናወናቸውንም አመልክተዋል። እንዲሁም ሁሉንም የኀብረተሰብ ክፍሎች የሚወክሉ 1 ሺህ 521 የልየታ ኮሚቴዎችና 1 ሺህ 186 የቅሬታና የአቤቱታ ኮሚቴዎች መመረጣቸውን ገልጸዋል። ለተመረጡ የልየታ ኮሚቴዎች ስልጠና የተሰጣቸው ሲሆን የቤት ለቤት ምዝገባ ለማካሄድ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች መሰራጨታቸውን አቶ ንጋቱ ተናግረዋል። ቀደም ሲል በአስሩ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ዘጠና ወረዳዎች በአንደኛና በሁለተኛ ዙር በተካሄደው ፕሮግራም 323 ሺህ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኀብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል። በሁለት ዙር በተከናወነው ፕሮግራም 602 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን የገለጹት የቢሮ ኃላፊው ከገቢያቸው 20 በመቶ በመቀነስ 95 ሚሊዮን ብር መቆጠባቸውንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም