በትግራይ ክልል በቤተሰብ ጤና ፓኬጆች አተገባበር ላይ አበረታች ስራ ተከናውኗል---ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር

59
ጥቅምት 13/2011 በትግራይ በቤተሰብ ጤና ፓኬጆችና በጤና መድህን አተገባበር ላይ ዓርአያነት ያለው ስራ መከናወኑን የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን አስታወቁ። ነገ በመቀሌ ከተማ የሚካሔደው 20ኛው ሃገር አቀፍ የጤና ዘርፍ ልማት ጉባኤ ተሳታፊዎች በክልተ አውላሎ ወረዳ የጤና ልማት ስራዎችን ጉብኝተዋል። ሚኒስትሩ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ ክልተ አብላዕሎ ወረዳ በገማድ፤በነጋሽና አብረሃ ወአፅበሃ  ቀበሌ ገበሬ ማህበራት እየተካሄደ ያለውን የቤተሰብ ጤና ፓኬጅና የጤና መድህን  አፈጻጸም  አድንቀዋል፡፡ ማህበረሰቡ የጤና መድህን ተጠቃሚ ቢሆንም የግልና የአከባቢ ንጽህና በመጠበቅ ረገድ የተሻለ ልምድ ስላለው ለህክምና ወደ ጤና ተቋማት መሄድ የሚያጠፉት ጊዜ አለመኖሩን  ተናግረዋል፡፡ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የታዩትን መልካም ተሞክሮዎች ወደ ሌሎች የክልሉና የሃገሪቱ አካባቢዎች ለማስፋፋት  እንደሚሰራም ጠቁመዋል። የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሃጎስ ጎደፋይ በበኩላቸው “በተወሰኑ ወረዳዎች ያለው የጤና ፓኬጅ አፈጻጸም ህብረተሰቡ ከተላላፊ በሽታዎች ራሱን መጠበቅ እንደሚችል ማሳያዎች ናቸው” ብለዋል፡፡ ሆኖም ሌሎች ቀበሌ ገበሬ ማህበራትና ወረዳዎች ተመሳሳይ አፈጻጸም እንዲኖራቸው ብዙ መሰራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡ በቀሪ የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አመታት የክልሉ የቤተሰብ የጤና ፓኬጅና ጤና መድህን ሽፋን ከ26 ወደ 65 በመቶ ለማድረስ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል። በክልተ አውለአሎ ወረዳ ገማድ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ ወይዘሮ ሙሉ ገብረስላሴ የጤና ፓኬጁን በባለሙያ እገዛ አማካኝነት በመተግበራቸው ከተላላፊ በሽታዎች ለመከላከል እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ ከዚሁ በተጨማሪ በአካባቢያቸው የሚገኙ 30 የቤተሰብ ኃላፊዎች የሳቸውን ተሞክሮ እንዲወስዱ በማድረግ እያገዙ መሆናቸውን ጠቁመው ለጤና መድህን በየዓመቱ 240 ብር ቢከፍሉም ለህክምና ወደ ጤና ተቋም ሂደው እንደማያውቁ ገልጸዋል፡፡ “የጤና ባለሞያዎች የሚሰጡንን የጤና ትምህርት ተግባራዊ በማድረግ በልማት ላይ ውጤታማ እንድንሆን አስችሎናል”ያሉት ደግሞ የቀበሌ ገበሬ ማህበሩ ነዋሪ አርሶ አደር ገብረሂወት አብረሀ ናቸው፡፡ የመኖሪያ አካባቢያቸውን በንጽሕና ከመጠበቅ ባለፈ የቆሻሻ አወጋገድና የእንስሳት አያያዝ ላይ ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረጉ በመሆናቸው ከስጋት መዳናቸውን ተናግረዋል። በጉብኝቱ ላይ የክልሉን የዘርፉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጨምሮ ከፌዴራልና ከክልሎች            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም