ኖርዌይ በኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲስፋፋ እደግፋለው አለች

43
አዲስ አበባ ጥቅምት 13/2011 ኖርዌይ በኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲስፋፋ ድጋፍ ለማድረግ ከመንግሥት ጋር ተስማማች። ሥምምነቱ በተለይም በጅማሮ ላይ ያሉ የንግድ ሥራዎች ሊጠናከሩ በሚችሉበት ጉዳዮች ላይ በትብብር መሥራትን ያካትታል ተብሏል። ሥምምነቱን የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያና የኑርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄንስ ፍሮሊች ፈርመውታል። ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ሥምምነቱ ወጣቶችን የሥራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ድጋፍ ለማግኘትም ያስችላል። በተለይም በአሁኑ ወቅት ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከግምት በማስገባት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት እድል እንደሚሰጥም ተናግረዋል። የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጄንስ ፍሮሊች በበኩላቸው መንግሥታቸው በኢትዮጵያ በጅምር ላይ ያሉ ኩባንያዎች በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑንም ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለማሳደግ የሚያስችል እድል መኖሩን ጠቁመው ይህንን ይበልጥ ከዳር ለማድረስ እንተባበራለን ብለዋል። ሚኒስትሩ አክለውም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው መንግሥትም የዲጂታል ዘርፉን ለማስፋት ያለው ቀጠርጠኝነትንም አድንቀዋል። በተለይም የሴት አመራር ሹመት፣ እየተወሰዱ ያሉ ፖለቲካዊና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችንና ከኤርትራ ጋር የተጀመረውን ሰላም ጨምሮ በቀጠናው እየታዩ የሚገኙ አዎንታዊ ለውጦችን አድንቀዋል። በተያያዘ ዜና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ዛሬ በኖርዌይ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራ ከፍተኛ ልዑክን ቡድንን አወያይተዋል። ሚኒስትር ዴኤታው በውይይቱ በአገራችንና በቀጠናው እየታዩ ስለሚገኙ አዎንታዊ ለውጦች ገለጻ አድርገው ሁለቱ አገሮች በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርናና በአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ያላቸውን ጠንካራ ትብብር አነስተው መወያያታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም