''የቤንዚን አቅርቦት እጥረት ሥራችንን እንዳናከናውን አድርጎናል''-የሶዶ ከተማ ታክሲ አሽከርካሪዎች

70
ሶዶ ጥቅምት 13/2011 በከተማዋ የተከሰተው የቤንዚን አቅርቦት እጥረትና የስርጭት ፍትሃዊነት መጓደል ሥራችንን በአግባቡ እንዳናከናውን አድርጎናል ሲሉ የወላይታ ሶዶ ከተማ ታክሲ አሽከርካሪዎች ተናገሩ፡፡ በከተማዋ በተለይ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ በነዳጅ ማደያዎች አካባቢ ረጃጅም ሰልፍ ይዘው ተራ የሚጠብቁ ተሽከርካሪዎችን ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ አሽከርካሪዎቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በከተማዋ የቤንዚን አቅርቦት እጥረትና የስርጭት ፍትሃዊነት ጉድለት ይታያል፡፡ የሶዶ ከተማ ታክሲዎች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ስሞኦን በሰጡት አስተያየት በከተማዋ በገጠመው የቤንዚን እጥረት ታክሲዎች አገልግሎታቸውን በተሟላ መልኩ እንዳይሰጡ ማድረጉን ይናገራሉ፡፡ የአንዳንድ ነዳጅ  ማደያዎች አገልግሎት አሰጣጥም ፍትሃዊነት ይጎድለዋል ይላሉ፡፡''ማደያዎቹ ሲፈልጉ ቀን ዘግተዉ ማታ የሚከፍቱ ወይም ለሚያውቁት አሽከርካሪ ቀድተዉ ሌላውን የሚከለክሉ በመሆናቸው መንግሥት ቁጥጥርና ክትትል ሊያደርግባቸው ይገባል'' በማለትም ያሳስባሉ፡፡ ማህበሩ በችግሩ ዙሪያ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በተደጋጋሚ ቢነጋገርም፤ ዘላቂ መፍትሄ አለማግኘቱን ሊቀመንበሩ ገልጸዋል። ወጣቱ የታክሲ አሸከርካሪ አማኑኤል በቀለ በበኩሉ በከተማዋ ባለው የቤንዚን እጥረት ሳቢያ አንድ ሊትር እስከ 35 ብር በችርቻሮ ለመግዛት በመገደዱ ለማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ችግሮች መዳረጉን ገልጿል፡፡ በችርቻሮ የሚሸጡ ግለሰቦች በጀሪካን ገዝተው ዋጋውን እጥፍ  እያደረጉ ሲሸጡ እየታየ በማደያዎች ቤንዚን የሚታጣበት ምክንያት ግልጽ ባለመሆኑ የሚመለከተው አካል ችግሩን ተከታትሎ ሊፈታው እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ ሌላኛው የባጃጅ  ታክሲ አሽከርካሪ ወጣት ሃቢብ ጀማል በከተማዋ ከነሐሴ 2010 ጀምሮ የተፈጠረው ቤንዚን እጥረት መከሰቱን ይገልጻል።ቤንዚን በማደያዎች እያለ ''የለም'' ብለው የሚከለክሉ ማደያዎች መኖራቸውንም  አስረድቷል፡፡ የሶዶ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሰለ ሶርሳ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የታክሲ አሸከርካሪዎች አቤቱታ ትክክል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በከተማው ያጋጠመው የቤንዚን እጥረት መንስዔ የአቅርቦትና የፍላጎት አለመመጣጠን ሲሆን፣የቤንዚን አመጣጥ ወጥነት አለመኖሩም ችግሩ እንዲባባስ አድርጎታል ብለዋል፡፡ በከተማው ለአንድ ወር ያህል ያጋጠመውን የቤንዚን እጥረት በዘለቄታው ለማቃለል መሥሪያ ቤታቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በአንዳንድ ማደያዎች የሚስተዋለዉን ፍትሐዊነት የጎደለው አገልግሎት አሰጣጥና ግለሰቦች በጀሪካንና በበርሜል ቤንዚን በመቅዳት በስርጭት ላይ ችግር መፍጠራቸው እውነት ነው ብለዋል። በመሆኑም ችግሩን ለማረም ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን ክትትል በማድረግና ሕጋዊ እርምጃዎችን በመከተል ከባለሃብቶችና ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ በሶዶ ከተማ ዘጠን የነዳጅ ማደያዎች ይገኛሉ፡፡              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም