በክልሉ ከ77 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የምገባ መርሀ ግብር ሊጀመር ነው

93
ባህር ዳር ጥቅምት 13/2011 በአማራ ክልል በተያዘው የትምህርት ዘመን 77 ሺህ 220 ችግረኛ ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የትምህርት ቤቶች የምገባ መርሀ ግብር ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን  የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። ለመርሀ ግብሩ ማስፈፀሚያ 20 ሚሊዮን ብር መመደቡንም ቢሮው ገልጿል። በቢሮው የስርዓተ-ምግብ ባለሙያ አቶ ተዋበ አለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት መርሀ ግብሩ የሚካሄደው ችግረኛ ተማሪዎች በምግብ እጥረት ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ለመታደግ ነው። በመጪው ህዳር 1 ቀን 2011 ዓ.ም ለሚጀመረው መርሀ ግብር ተጠቃሚ ተማሪዎችን የመለየትና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ ይገኛሉ። እንደ ባለሙያው ገለጻ የምገባ መርሀ ግብሩ የሚካሄደው በሰሜን ጎንደርና ዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች በሚገኙ 407 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው። በክልሉ ችግረኛ ተማሪዎች በምግብ እጥረት ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ እየተደረገ ባለው ድጋፍ  ባለሀብቶችና በጎ አድራጎት ድርጅቶች የድርሻቸውን እንዲወጡም ባለሙያው ጥሪ አቅርበዋል። በተያዘው የትምህርት ዘመን በክልሉ በ8 ሺህ 900 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ መሆናቸው ታውቋል ።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም