በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ ትብብር ተጠየቀ

63
አዲስ አበባ ጥቅምት 11/2011 በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች ሰብአዊ እርዳታ ለማድረግ የተባበረ ጥረት እንዲደረግ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የስነ ህዝብ ፈንድ ጥሪ አቀረበ። የቻይናው ዜና አገልግሎት (ዥኑዋ) እንደዘገበው፤ የፈንዱ የስራ ሃላፊዎች ትናንት በጋምቤላ የሚገኘውን የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ሲጎበኙ ነው ትብብሩ የተጠየቀው። በደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ምክንያት 423 ሺህ ስደተኞች በጋምቤላ መጠለያ እንደሚገኙ በዘገባው ተገልጿል። የስነ ህዝብ ፈንድ መረጃ እንደሚያሳየው በጋምቤላ መጠለያ ካምፕ የሚኖሩ ስደተኞች ውስጥ 64 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ18 አመት በታች ሲሆኑ 88 በመቶ ደግሞ ሴቶችና ህጻናት ናቸው። በመጠለያ ካምፑ የማህበራዊ አገልግሎት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን የገለጸው ፈንዱ በዚህም ስደተኞቹ አገልግሎቱን ያለማግኘት ስጋት ውስጥ መግባታቸውን ገልጿል። በመጠለያው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግም ፈጣን ጥረት እንደሚያስፈልግ በመጠቆም በተለይም ለእናቶች ጤና አገልግሎት ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ተነግሯል። በጋምቤላ ክልል የሚገኘው አንድ ሪፌራል ሆስፒታል ብቻ በመሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እናቶች አሁንም ቤት ውስጥ እየወለዱ ነው። በመሆኑም ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች እና ህጻናትን ለመታደግ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ዥኑዋ በዘገባው አስፍሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም