ወጣቱ በቀዶ ህክምና 127 ሚስማሮችና ሌሎች ባዕድ ነገሮች ተወገደለት

64
አዲስ አበባ ጥቅምት 11/2011 በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ  ሆስፒታል ትላንት ሌሊት በተደረገ የቀዶ ህክምና 127 ሚስማርና ሌሎች ባእድ ነገሮች ከታካሚ ሆድ ውስጥ ማውጣት ተችሏል። ከሚስማሮች በተጨማሪ መርፌ፣ የተሰባበሩ ብርጭቆዎች የጥርስ ማጽጃ ስንጥሮች በቀዶ ህክምናው የተወገዱት ናቸውም ተብሏል። ኢዜአ በስፍራው በመገኘት ከወጣቱ  ሆድዕቃ በቀዶ ህክምናው የወጡ ባእድ ነገሮችን ተመልክቷል። ቀዶ ጥገናውን የመሩት በሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ዳዊት ተዓረ እንደገለጹት፤ የ33አመት እድሜ ያለው ወጣት በሆስፒታሉ በተደረገለት የቀዶ ህክምና በርካታ ባዕድ ነገሮች ከሆድቃው እንዲወጣ ተደርጓል። 2፡30 የፈጀው የቀዶ ህክምና ሰባት የህክምና ባለሙያዎች ተሳተትፈውበት የተካሄደና በስኬት የተጠናቀቀ እንደሆነ ተገልጿል። ታካሚው 'አኩፊጂያ' በተባለ የአእምሮ ህመም ላለፉት አስር አመታት ተጠቂ መሆኑን በመግለጽ ለስምንተ ዓመታት የአእምሮ መድሃኒት ሲወስድ መቆየቱንም ዶክተር ዳዊት አክለዋል። ይሁን እንጂ ህክምናውንና መድሃኒቱን አቋርጦ ለሁለት ዓመታት በጸበል ህክምና ሲረዳ መቆየቱን አስታውሰዋል። እንደ ዶክተር ዳዊት ገለጻ፤ ከቅርብ ቀናት በፊት  ወደ ሆስፒታሉ ለውስጥ ደዌ ህክምና በመጣበት አጋጣሚ ለአጠቃላይ ምርመራ የራጅ ህክምና ሲደረግለት በሆድቃው አካባቢ ባልተለመደ ሁኔታ የባእድ ነገሮች ምስል በመታየቱ ቀዶ ህክምና ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል። በዚህም ከ120 በላይ ሚስማሮችን ጨምሮ መርፌ፣ ስቴኪኒና የተሰባበሩ ጠርሙሶች በህክምናው እንዲወገድለት ተደርጎ በአሁኑ ወቅትም ወጣቱ በማገገሚያ ክፍል ውስጥ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ወጣቱ ሚስማሮችንና ባእድ ነገሮችን ሲጠቀም የነበረው ከወራት በፊት እንደሆነ በህክምናው መረጋገጡንም አክለዋል። ሌላው በቀዶ ህክምናው የተሳተፉት የልብ ሃኪምና የሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከሳንባና ከቲቢ ህክምና አገልግሎቶች በተጨማሪ ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው እንዲህ አይነት የቀዶ ህክምና አገልግሎት ስለሚሰጥ ህብረተሰቡ ማወቅ እንዳለበት ገልጸዋል። ትናንት ሌሊት የተካሄደው ቀዶ ጥገና በተሳካ ሁኔታ ተካሂዶ ታካሚው በማገገሚያ ክፍል በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በዚህም ሆስፒታሉ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የህክምና አይነቶች ላይ ህክምናዎችን የሚሰጥ በመሆኑ ህብረተሰቡ ወደ ሆስፒታሉ በመምጣት የህክምና አገልግሎቶችን በቀላሉ ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።  የአእምሮ ህሙማኖች መድሃኒታቸውን እንዳያቋርጡና በሽታው እያገረሸ ለባሰ የጤና እክል እንዳይጋለጡ ቤተሰብ በቅርበት ሊከታተክል እንደሚገባ ባለሙያዎቹ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም