ህገ-ወጥ የቡና ንግድና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይፈቱልን---በጌዴኦ ዞን ባለሀብቶች

108
ዲላ ጥቅምት 11/2011 በጌዴኦ ዞን ለልማት እንቅፋት የሆኑ ህገ-ወጥ የቡና ንግድና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱላቸው ባለሀብቶች ጠየቁ። በዞኑ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስፋፋት ያለመ የምክክር መድረክ ትላንት በዲላ ከተማ ተካሂዷል ። በምክክር መድረኩ የተሳተፉ ባለሀብቶች እንደገለፁት ህገ-ወጥ ንግድ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የመሰረተ ልማት አለመስፋፋት ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ተግዳሮቶች ናቸው ። በቡና አቅራቢነት ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ተስፋዬ ጎቻ በሰጡት አስተያየት በዞኑ የሚስተዋለው ህገወጥ የቡና ንግድ በሥራቸው ላይ ጫና ፈጥሮባቸዋል። ቡናን ለገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ በሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ለመሰማራት ቢፈልጉም ከመሬት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንቅፋት እንደሆነባቸው ጠቁመዋል ። በቡና፣ በሆቴልና መጠጥ ንግድ የተሰማሩት አቶ አየለ ደጉ በበኩላቸው ከማዘጋጃ ቤት አሰራር፣ ከመንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ጋር የተያያዙ ችግሮች በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። የዞኑ አስተዳደር ከባለሀብቱ ጋር በመቀራረብ ችግሮቹን እንዲፈታ ባለሀብቶቹ ጠይቀዋል ። የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ በበኩላቸው ከባለሀብቱ የተነሱ የመሰረተ ልማት፣ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ተግዳሮቶችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል ። "አንዳንድ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶችም የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዳይስፋፋ እንቅፋት የሆኑበት አጋጣሚ ያለ በመሆኑ ወደ ትክክለኛ መስመር እንዲገቡ ይደረጋል" ብለዋል ። ዞኑ በአለም አቀፍ ደረጃ በጣዕሙ ተፈላጊ የሆነ ቡና የሚመረትበት ቢሆንም ቡናን እሴት ጨምሮ በማምረት ለገበያ በማዋል የተሻለ ገቢ ለማግኘት የሚያስችል ኢንዱስትሪ በአካባቢው አለመኖሩን ጠቁመዋል ። እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ ዞኑ ለጥምር ግብርና፣ ለፍራፍሬ ልማትና ለከብት ርቢ አመቺ በመሆኑ ባለሀብቱ በእነዚህ አማራጮች ላይ በስፋት እንዲሰማራ በትኩረት ይሰራል። የንብ ማነብ፣ ደን ልማትና ቱሪዝም ሌሎች ምቹ አማራጮች መሆናቸውን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው ባለሀብቱ በስፋት እንዲሳተፍባቸው የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል። የዞኑ ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ዩኒት አስተባባሪ አቶ አብዮት ማሞ በዞኑ 188 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 301 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ተናግረዋል ። " ፕሮጀክቶቹ ለ5 ሺህ 440 ሰዎች ቋሚና ለ22 ሺህ 424 ሰዎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል" ብለዋል ። ፡፡ በዞኑ በሦስት ወረዳዎች በግንባታ ላይ ያሉ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ዞኖች ለአካባቢው ኢንቨስትመንት መነቃቃት ምቹ አጋጣሚ መፍጠራቸውን ገልፀዋል ። አቶ አብዮት እንዳሉት በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት ከባለሀብቱና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር  በትብብር ይሰራል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም