በዞኖቹ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተው ግጭት በሰላም እንዲፈታ ነዋሪዎች ጠየቁ

65
ነቀምት ጥቅምት 11/2011 በቤኒሻጉል ጉሙዝ ካማሼና በምስራቅ ወለጋ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት በሰላም እንዲፈታ የተለያተዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጠየቁ። ከነቀምት ከተማ የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ትላንት በሰላም ጉዳይ ላይ ውይይት አካሄደዋል። የህብረተሰብ ክፍሎቹ በወቅት ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት የፌዴራል መንግሥትና የክልሎቹ አስተዳደሮች ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ተገቢ ትኩረት ስጥተው መስራት ይጠበቅባቸዋል ። በነቀምት ከተማ ቀበሌ 03 ነዋሪና የአገር ሽማግሌ አቶ ከበደ ዱፌራ የሁለቱ ክልሎች ነዋሪዎች ለበርካታ ዓመታት በሰላም አብረው የኖሩና የተዛመዱ መሆናቸውን ተናግረዋል። በአገሪቱ የመጣውን ለውጥና የዜጎችን አንድነት የማይፈልጉ ኃይሎች በለኮሱት እሳት ለሠላማዊ ዜጎች ህይወት መጥፋትና መፈናቀል ምክንያት እየሆነ በመምጣቱ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ግጭቱን ባፋጣኝ እንዲያቆሙ ጠይቀዋል። መንግስት ታጣቂዎቹን ትጥቅ በማስፈታት በክልሎቹ ሠላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባም አመልክተዋል። ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አቶ ኤቢሣ ጉያሳ በበኩላቸው “ተከስቶ የነበረው ግጭት በሕዝቡ የእለት ተእለት ኑሮ ላይ ሥጋት በመፍጠሩ በአካባቢዎቹ ሠላምና መረጋጋት እንዲፈጠር መንግሥት የሕግ የበላይነትን ሊያስከብር ይገባል “ ብለዋል ። “የታጠቀው ክፍል በሰላማዊ ሕዝብ ላይ እየወሰደ ያለው የማፈናቀልና የመግደል እርምጃ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም” ያሉት ደግሞ በነቀምት ከተማ የቀበሌ 05 ነዋሪ ኮማንደር ደሳለኝ በልአ ናቸው። የክልልና የፌዴራል አካለት መንግስት አጥፊዎችን በመከታተልና ለሕግ ከማቅረብ ባለፈ ለዘላቂ ሰላም ሊሰራ እንደሚገባ ጠይቀዋል። የኦሮሚያ የጤና ቢሮ ኃላፊና የኦሮሞ ዲሞክራሲዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ዶክተር ደረጀ ዱጉማ  ብሔር ብሄረሰቦችን በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሯሯጡ ኃይሎችን መንግስት ተከታትሎ ለሕግ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ። በአካባቢዎቹ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ህዝቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ዶክተር ደረጀ ጥሪ አቅርበዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም