የተከራየነው ቤት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለሽያጭ መቅረቡ ስጋት ፈጥሮብናል...በሰቆጣ የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎች

50
ሰቆጣ ጥቅምት11/2011 የምንኖርበት የኪራይ ቤት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለሽያጭ መቅረቡ የእለት ተእለት ኑሯችንን ተረጋግተን እንዳንመራ አድርጎናል ሲሉ በሰቆጣ የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎች ቅሬታቸውን አቀረቡ። በጋራ መኖሪያ ቤቶች በኪራይ የሚኖሩ ዜጎች ድንገት ልቀቁ መባላቸውን እውቅና እንደሌለው ከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡ ከቅሬታ አቅራቢዎች መካከል ወይዘሮ ሃበሻ በላይ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ከአማራ ክልል ቤቶች ልማት ድርጅት ሰቆጣ ቅርንጫፍ ጋር በየዓመቱ ውል ገብተው በሰቆጣ ከተማ በሚገኘው "አዝባ የጋራ መኖሪያ ቤት"  በኪራይ እንደሚኖሩ ተናግረዋል። በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በአነስተኛ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተደረገው መሰረት እርሳቸውም በጡረታ በወር ከሚያገኙት 600 ብር 524 ብር ለቤት ኪራይ እየከፈሉ ሲኖሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል። "እየኖርንበት ያለው የጋራ መኖሪያ ቤት በቤቶች ልማት ኤጀንሲ ለሽያጭ ቀርቧልና መልቀቅ አለባችሁ መባሉ ጭንቀት ከመፍጠሩ ባለፈ ኑሯችንን በተረጋጋ መንፈስ እንዳንመራ አድርጎናል‘’ ብለዋል፡፡ ‘’የጋራ መኖሪያ ቤቱን ለመግዛት አቅም የሌለን የመኖሪያ ዕጣ ፋንታችን ምን ሊሆን ይችላል‘’ ሲሉ የሚጠይቁት ደግሞ በተለምዶ ቄራ ተብሎ በሚጠራው የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪ የሆኑት አቶ ደሳሉ በለጠ ናቸው። "ከተከራዮች ጋር ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ ሳይደረስ ኤጀንሲው በራስ ፍላጎት ብቻ ተነሳስቶ እየኖርን ያለንበትን ቤት ለሽያጭ ማቅረቡ ተገቢ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ስድስት ቤተሰቦችን እንደሚያስተዳድሩ የገለጹት አቶ ደሳሉ፣ እስከዛሬ አቅምን ባገናዘበ የቤት ኪራይ ተጠቃሚ ብሆንም ቤቱ ለሽያጭ ቀርቧልና ልቀቁ መባሉ በቤተሰቦቻቸው ላይ ድንጋጤን መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ በጋራ መኖሪያ ቤቱ በኪራይ መልክ እንድንኖር ሲደርግ ያልተጠናቀቀና ቤት በመሆኑ ብዙ ነገሮችን በራሳችን ወጪ አሟልተናል ያሉት ደግሞ ደግሞ አቶ ፋንታው ስዩም የተባሉ ተከራይ ነዋሪ ናቸው፡፡ "በራሳችን ወጭ የቀለም፣ የውሃ እና የመብራት መስመሮችን እንዲሁም የበርና መስኮት መስታወት አሟልተናል፤ ይህ ሁሉ ግምት ውስጥ ሳይገባ የምንኖርበት ቤት ቤት ለሽያጭ ሊቀርብ  ነዉ መባሉ ተገቢ አይደለም" ብለዋል፡፡ በየዓመቱ የሚታደስ የቤት ኪራይ ውል ወስደን እየኖርን ቢሆንም ከተከራዮች ጋር በመነጋገር መግባባት ላይ ሳይደርስ  ቤቶቹ ለሽያጭ መቅረባቸው ጭንቀት ውስጥ እንዲገቡና እንዳይረጋጉ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ ወይዘሮ ግብፅ ሙላው በበኩላቸው " የግል መኖሪያ ቤት ስለገነባችሁ የያዛችሁት የኪራይ ቤት ተሸጧል፤ በ30 ቀናት ውስጥ እንድትለቁ ተብሎ በደብዳቤ ትዕዛዝ ሲደርሰኝ ድንጋጤ ፈጥሮብኛል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የሰሩት የግል መኖሪያ ቤት ያልተጠናቀቀ ከመሆኑም ባለፈ የውሃና የመብራት መስመር ያልተዘረጋለት በመሆኑ ይህንን ግምት ውስጥ ያላስገባ ውሳኔ በመወሰኑ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ በአማራ ክልል ቤቶች ልማት ድርጅት የሰቆጣ ቅርንጫፍ ተወካይ ኃላፊ አቶ ታምሩ እንግዳ በበኩላቸው በተገነቡ 354 ቤቶች አነስተኛ ገቢና በመንግስት ሥራ የሚተዳደሩ የህብረተሰብ ክፍሎ በኪራይ እየኖሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ክልሉ ባካሄደው ጥናት መሰረት በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ እየኖሩ ያሉና በስማቸው ቤት የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በረዥም ጊዜ ክፍያ ለሚኖሩበት ቤት ግዥ እንዲፈጽሙ ዕድል የተሰጣቸው መሆኑ ተናግረዋል፡፡ " በዚህ ሂደት አብዛኞቹ ተከራዮች ቤቱን ለመግዛት ፍላጎት ባለማሳየታቸው ከእዚህ ቀደም የመግዛት ፍላጎት ላሳዩ አካላት ግዥ እንዲፈፀሙ እየተደረገ ነው" ብለዋል፡፡ "በእስካሁኑ ሂደትም በኪራይ ያልተላለፉ አምስት መኖሪያ ቤቶች ሽያጭ እንዲፈጸሙ ተደረውጓል" ያሉት አቶ ታምሩ እንዲለቁ የተወሰነው የግል ቤት ገንብተው ያጠናቀቁ ተከራዮች እንጅ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ ተከራዮች አለመሆናቸውን አስረድተዋል። "የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለሽያጭ መቅረባቸውን አላውቅም"ያሉት ደግሞ የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዱኛው ወዳጅ ሁሉንም ተከራይ ባሳተፈና በመተማመን ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ማስቀመጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ተከራይተው የግል ቤት ሰርተው ያጠናቀቁ ግለሰቦች የውሃ እና የመብራት እንዲሁም የመንገድ መሰረተ ልማቶች እንዲሟል ከተማ አስተዳደሩ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከቤቶች ልማት አስተዳደር አካላት ጋር በመነጋገር የጋራ መፍትሄ አስኪቀመጥ ድረስ ተከራዮች ኑሯቸውን በተረጋጋ ሁኔታ እንዲመሩም ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም