በሲዳማ ሕዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ ሁለት ድርጅቶች በጋራ ለመሥራት ተስማሙ

64
ሐዋሳ  ጥቅምት 10/2011 የሲዳማ ብሄራዊ ነጻነት ግንባርና የሲዳማ አርነት ንቅናቄ/ሲአን/ በጋራ ለመሥራት መወሰናቸውን ዛሬ ገለጹ፡፡ ፓርቲዎቹ በሃገሪቱ የመጣው ለውጥ እንዳይቀለበስ ህዝቡ በተረጋጋና በሰከነ መንገድ እንዲንቀሳቀስ ጠይቀዋል፡፡ የሲዳማ ብሄራዊ ነጻነት ግንባር የውጭ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ደንቦባ ኪአ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ድርጅታቸው ከሲዳማ አርነት ንቅናቄ ጋር በጋራ በመንቀሳቀስ  ተስማምቷል።ለለውጡ ሂደት ቀጣይነትም  ይሰራል፡፡ ድርጅቱ ተቀናጅቶ ለመሥራት የወሰነው የሕዝብ ጥያቄ ተከትሎ መሆኑንና የሰላምና የዴሞክራሲ ሂደቱን ለመገንባት እንደሚቻል በማመኑ ነው ብለዋል። የሲዳማ አርነት ንቅናቄ/ሲአን/ሊቀመንበር አቶ ዱካሌ ላሚሶ በበኩላቸው ድርጅቶቹ በጋራ ለመሥራት የተስማሙት ተመሳሳይ ዓላማና ግብ ያላቸውና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ስምምነቱ በአገር ውስጥም በውጭም በጋራ ለመንቀሳቀስ እንደሚያስችላቸውና በሂደትም ወደ ውህደት ለማምራት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል። ይህም ድርጅቱ በቀጣዩ ምርጫ ለመሳተፍ  እያደረገ ባለው ዝግጅት ውህደቱ የተሻለ አቅም እንደሚፈጥርለትም ሊቀመንበሩ ተናግረዋል። የሲዳማ ሕዝብ በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ በመደገፍ ላይ እንደሚገኝና መነቃቃትን እንደፈጠረለት በቅርቡ በስድስት ወረዳዎች ባደረጓቸው ስብሰባዎች ማረጋገጣቸውን ኃላፊዎቹ ገልጸዋል። በየደረጃው የሚገኙት አመራሮችና ሕዝቡ ለውጡን እየገጠሙት ያሉትን ተግዳሮች በተረጋጋና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ለመወጣት እንዲንቀሳቀሱ ጠይቀዋል፡፡ ከውጭ የገቡ ፖለቲካ ፓርቲዎችም የለውጡ ደጋፊዎችና የመፍትሄ አካል እንጂ፤ የችግሩ አካል  መሆን እንደሌለባቸውም አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም