ዩኒቨርስቲው አፍሪካን በስነ ህንጻ ንድፍና በምርምርና በቱሪዝም ዘርፍ የሚያስጠራ ነው—ምሁራን

4029

 

መቀሌ ሚያዝያ 22/2010 የዓድዋ ፓን አፍሪካን ዩኒቨርስቲ አህጉሪቱን በስነ-ህንፃ ንድፍ ፣በታሪክ፣ በምርምርና በቱሪዝም ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስጠራት መሆኑን ምሁራን ገለጹ፡፡

የአድዋ ፓን አፍሪካን ዩኒቨርስቲ አለም አቀፍ ኮንፍረንስ  ተሳታፊ የነበሩ ምሁራን እንዳሉት የዩኒቨርስቲው መገንባት አፍሪካውያን  የዓለም ምሁራን ትኩረት እንዲያገኙ  ያስችላል፡፡

ዶክተር እሸቱ ተመስገን  በአዳማ ዩኒቨርስቲ የምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ሲሆኑ ” የአድዋ ፓን አፍሪካን ዩኒቨርስቲ ከሌሎች ዩኒቨርስቲዎች  በይዘትም ሆነ በዓላማ ተለይቶ  የሚጎበኝ ዩኒቨርስቲ  ይሆናል “ሲሉ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው የስነ-ህንፃ ይዘቱ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተሰሩትን በሚያንፀባርቅ መልኩ ሊሆን  እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ዶክተር እሸቱ  እንዳሉት እሳቸውም የሚቋቋመው ዩኒቨርስቲው አስተባባሪዎች አባል እንደመሆናቸው ዋነኛ ትኩረታቸው የአህጉሪቱን  የስነ-ህንፃ  ስራዎች የዓለም የዘርፉ ምሁራኖች  ትኩረት እንዲስብ ተደርጎ ይሰራል፡፡

በጀርመን ሀገር  የማክስብላንክ የዓለም አቀፍ ሰላምና የህግ የበላይነት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር መሐሙድ አብዱላሂ  በበኩላቸው የአድዋ ድል የጥቁር ህዝቦች ነፃ ያወጣ በመሆኑ የሚቋቋመው የዓድዋ ፓን አፍሪካን ዩንቨርስቲ የዚሁ ተምሳሌት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

የዩኒቨርስቲው መቋቋም አፍሪካዊያን  የዓለም ምሁራን ትኩረት እንዲያገኙ  የሚያስችል መሆኑንም  ዶክተር መሐሙድ ገልጸዋል።

የኢኮኖሚክስ ምሁሩ  አቶ ንዋይ  ክርስቶስ ገብረአብ በሰጡት አስተያየት ” የዩኒቨርስቲው መከፈት አፍሪካ የአለም ጥቁር ህዝቦች ተምሳሌነቷን  ይበልጥ የሚያጎላ ነው “ብለዋል።

ለዘመናት ምንም ሳይሰራባቸው የቆዩት የዓድዋ ተራሮችም ከፍተኛ የቱሪዝም መስህብ በመሆን ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት የበኩለሉን አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቅሰዋል፡፡ ፡፡

 በአድዋ ስያሜ  የሚገነባው የፓን አፍሪካን ዩኒቨርስቲ አህጉሪቱን በስነ ህንፃ ንድፍ ፣በታሪክ፣ በምርምርና በቱሪዝም ዘርፍ  በዓለም አቀፍ ደረጃ  እንደሚያስጠራት ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት፡፡