ኀብረተሰቡ ደጋፊ ያጡ ህፃናትና አረጋውያን በመርዳት እንዲተባበር ጥሪ አቀረበ

70
አዲስ አበባ ጥቅምት 10/2011 ኀብረተሰቡ ደጋፊ የሌላቸውን ህፃናትና አረጋውያን በመርዳት እንዲተባበር የህፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት ጥሪ አቀረበ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስር የሚገኘውና 45ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን የሚያከብረው ድርጅቱ ከ25 ሺህ 900 በላይ ህፃናትና ቤተሰቦቻቸውን ሲደግፍ ቆይቷል። በድርጅቱ 19 ማዕከላት ለ479 ህፃናት የምግብ፣ የአልባሳት፣ የትምህርትና ሌሎች ድጋፎችን እንዲሁም ከቤተሰባቸው አንዱን በሞት ላጡ 14 ሺህ 745 ህፃናት የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ ያደርጋል። ለህጻናቱ ቤተሰቦች የብድር አገልግሎት በመስጠት ሰርተው ራሳቸውን እንዲችሉ እያደረገ መሆኑንም የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ቀሲስ ሳምሶን በቀለ ገልጸዋል። በተጨማሪም ከ11 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ህፃናትና ቤተሰቦቻቸው የትምህርትና የስልጠና አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን 577 ህፃናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙም አድርጓል። በማህበሩ የእስካሁን እንቅስቃሴ ድጋፍ የተደረገላቸው ህፃናት ቁጥር ከ40 ሺህ በላይ መሆኑን የጠቀሱት ቀሲስ ሳምሶን ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑት በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች ተመርቀው ስራ መያዛቸውን አውስተዋል። ድርጅቱ ዛሬ 45ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በማስመልከት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን 37ኛው የሰበካ ጉባዔ መደበኛ ስብሰባ ተካፋይ ለነበሩ 500 አባቶችም የዓይን፣ የስኳርና የደም ግፊት ምርመራ አድርጓል። የምስረታ በዓሉን አስመልክቶ ከሚከናወኑ መርሃ ግብሮች መካከል አባቶች በድርጅቱ ስር የሚገኘውን የምግባረ ሰናይ ጠቅላላ ሆስፒታል እንዲጎበኙና የጤና ምርመራም እንዲያካሂዱ ማድረግ ነው። ይህም አባቶች የድርጅቱን የበጎ አድራጎት ተግባር ለኀብረተሰቡ በማስረዳት እገዛ እንዲያደርግ የማስተባበር ስራ እንዲሰሩ ለማድረግ ታስቦ መሆኑን ዋና ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል። ኀብረተሰቡ የኢትዮጵያውያን ችግር የሚፈታው በኢትዮጵያውያን መሆኑን ተረድቶ ድርጅቱን እንዲያግዝም ጥሪ አቅርበዋል። በሆስፒታሉ የተገኙት የሰበካ ጉባዔው መደበኛ ስብሰባ ተካፋዮች የድርጅቱን መልካም ስራ ለማጎልበት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል። የካሊፎርኒያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አባ ኤዎስጣቴዎስ አረጋዊያንና ህፃናትን መርዳትና ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ መልካም ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል። በድርጅቱ የተጀመረውና ቤተክርስቲያኗ እያከናወነችው ያለውን በጎ ጅምር ለማጎልበት ኀብረተሰቡ ሊተባበር እንደሚገባ ገልጸው ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንደሚያበረክቱ ገልፀዋል። የአቃቂ ቃሊቲ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሰበካ ጉባዔ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው አበበ በበኩላቸው አቅመ ደካሞች እንዲረዱና የአገሪቱ የነገ ተስፋ የሆኑ ህፃናት ድጋፍ እንዲያገኙ በየደብሩ በሚከናወኑ መርሃ ግብሮች ቅስቀሳ ሊደረግ ይገባል ብለዋል። "በእኔ በኩል የማስተባበር ስራ እሰራለሁ" ያሉት አቶ ጌታቸው ሁሉም ዜጋ በችግር ላይ ያሉ ወገኖቹን እንዲንከባከብ ጠይቀዋል። ከተመሰረተ 45 ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ ድርጅት ምግባረ ሰናይ ጠቅላላ ሆስፒታልን ጨምሮ ባሉት 19 ማዕከላት ለህፃናትና ቤተሰቦቻቸው የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ይገኛል። ድርጅቱ 45ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ዛሬ ባካሄደው የአባቶች የጤና ምርመራ የጀመረ ሲሆን ከጥቅምት 14-18 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄድ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይት እንደሚያከብር ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም