ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ይገባል ተባለ

77
አዲስ አበባ ጥቅምት 10/2011 በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭት መቀነስ እንዲቻል የማህበረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ የጤና ባለሙያዎች ገለፁ። በመላው ዓለም ከሚጠቀሱት ዋነኛ የሞት ምክንያቶች የኩላሊት ስራ ማቆም፣ የልብ ድካም፣ ስኳር፣ የመተንፈሻ አካላትን ጨምሮ ሌሎችን ያካተቱት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ። የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው ሪፖርት በአውሮፓዊያኑ 2016 ብቻ ከ40 ሚሊዮን በላይ የዓለም ህዝብ በበሽታዎቹ ሳቢያ ለሞት ተዳርጓል። የልብ ህመም፣ ካንሰር፣ የመተንፈሻ አካላት እንዲሁም የስኳር ህመሞች ከፍተኛውን ድርሻ የያዙ የሞት ምክንያቶች ናቸው። በኢትዮጵያም እነዚህ በሽታዎች 30 በመቶ ለሚሆን ህዝብ ሞት ምክንያት እንደሆኑ ነው የአለም ጤና ድርጅት መረጃ የሚያመለክተው። በበሽታዎቹ የተጠቁትን ህይወት ለመታደግ ለህክምና የሚወጣው ወጪም እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ጥናቶች ያስረዳሉ። የሽታዎቹን ስርጭት እና ጉዳት ለመቀነስ ስለሽታዎቹ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ ወሳኝ እንደሆነ የጤና ባለሙያዎቹ ለኢዜአ ሪፖርተር ገልፀዋል። ለሽታዎቹ ከሚያጋልጡት ምክንያቶች መካከል የአኗኗር ዘዬና የአመጋገብ ባህል መሰረታዊዎቹ እንደሆኑ የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ሀኪሙ ዶክተር ምትኩ ገብረጊዮርጊስ ያብራርተዋል። በመሆኑም የሽታዎቹን ምንነት፣ የህይወትና አካላዊ አደጋ እንደዚሁም ባህሪያትና መከላከያ መንገዶቹን በተመለከተ የህዝቡን እውቀት ማሳደግ ስርጭቱንም ሆነ ጉዳቱን ለመቀነስ እንደሚያግዝ አመልክተዋል። ጠቅላላ ሀኪም የሆኑት ዶክተር ታምሩ መልካ በበኩላቸው በአገሪቱ የጤና ጥበቃ ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት ህዝቡን ከማስተማር ጎን ለጎን በሽታዎቹን ለመከላከል የሚያስፈልጉ የህክምና መስጫ ተቋማትንና መሳሪያዎችን ማጠናከር እንዳለባቸው ተናግረዋል። ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች በህብረተሰቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ሞት ለመቀነስ የግንዛቤ ስራ እየተሰራ መሆኑን የሚገልፁት ደግሞ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቡድን የአይን ህክምና አስተባባሪ ዶክተር ሶስና ኃይለማርያም ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት መስሪያ ቤታቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን እያዘጋጀ በሽታዎቹን የመከላከል ተግባር እያከናወነ ነው። ወደፊትም በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አማካኝነት እየተሰጠ ያለው የጤና ትምህርት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል። መንግስት የህክምና ግብዓቶችን ለሟማላት የሚያደረገውን ጥረት ሁሉም ህብረተሰብ እንዲደግፍም ጥሪ አስተላልፈዋል። ማህበረሰቡ አዘውትሮ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግና የአመጋገብ ስርዓቱን በማስተካከል የሽታዎች ስርጭት መቀነስ  እንደሚችል ነው ባለሙያዎቹ የመከሩት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም