በትግራይ ክልል በሁሉም ዘርፎች መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ አዲስ አደረጃጀት ይፈጠራል- ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል

69
መቀሌ ጥቅምት 10/2011 በትግራይ ክልል በሁሉም ዘርፎች መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት አዲስ አደረጃጀት እንደሚፈጠር የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል አስታወቁ። ምክር ቤቱ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆየው የአምስተኛ ዘመን 13ኛ መደበኛ ጉባዔ ዛሬ ጀምሯል። የምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በ2011 በጀት ዓመት ዋና ዋና ዕቅዶችንና የትኩረት አቅጣጫዎችን አቅርበዋል። ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣በክልሉ የተረጋጋ ምጣኔ ሀብት  ለማምጣት፣በስፋት የሚታዩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት መሰረታዊና አዲስ ለውጥን ማምጣት ያስፈልጋል። ትርጉም ያለው ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣትም በበጀት ዓመቱ በተለየ ሁኔታ ሪፎርም ይደረጋል ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን፣ለ20 ዓመታት ሥራ ላይ የነበረውን የክልሉ የመንግሥት አደረጃጀት በሁሉም ዘርፎች በአዲስ ይደራጃል ብለዋል። አደረጃጀቱን በመስራትም የክልሉ የድህነት መጠንን አሁን ካለበት 29 በመቶ  በሁለት በመቶ የመቀነስና በተመሳሳይ መልክ የስራ አጥነት መጠንም ከ17 በመቶ በታች ለማውረድ እንደሚያግዝ ገልጸዋል። የተያዘው በጀት ዓመት የተደራረቡ ሥራዎች የሚከናወንበት ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣የሴቶችና ወጣቶች ተጠቃሚነትን የማስፋት፣የተፈናቀሉ ወገኖችን የማቋቋም፣ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየበትን የሁለተኛው ዘመን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድን በተሻለ ሁኔታ ለማከናወን የህዝብ ተሳትፎ ርብርብ የሚደረግበት ነው ብለዋል። በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ጸጋዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ርብርብ እንደሚደረግና በዚህም የመቀሌ፣ሑመራና ደቡባዊ ዞኖች የልማት ኮሪዶሮች ሥራ  እንዲጀምሩ በጥናት መለየታቸውን አመልክተዋል። በክልሉ የተሟላ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት ትምህርትን በስፋት የማዳረስ ሥራ እንደሚከናወኑና ጥናትና ምርምርን መሰረት ያደረጉ ተግባራትን በሁሉንም  የክልሉ መንግሥት ሥራዎች ለማካተት መታቀዱን አስረድተዋል። በክልሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትና ያልተማከለ አስተዳደርን የሚያረጋግጡ ተግባራት የሚከናወኑ ሲሆን፣ሁሉም ስራዎች በውጤት እንዲለኩ እንደሚደረግም ገልጸዋል። በውጤቱ  መሰረትም ሁሉም የመንግስት ሰራተኞች ይለካሉ፣በአግባቡ ኃላፊነቱን ያልተወጣ ሰራተኛም ይጠየቃል ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ። በክልሉ ትኩረት ተሰጥቶባቸው የለውጥ ሥራ ከሚካሄድባቸው ተቋማት መካከልም የክልሉ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ፣የመገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ እንደሚገኙባቸው የጠቀሱት ዶክተር ደብረጽዮን፣የማህበራዊ ሚዲያ ዘርፍም ትክክለኛ ሃሳብና መረጃ እንዲያቀርብ  ይጠናከራል ብለዋል። በክልሉ ነጻ የህዝብ አደረጃጀቶችና የሲቪክ ማህበራት እንዲኖሩ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በግብርና፣ትምህርት፣ጤና በከተሞች የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ላይ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚከናወኑ  ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል። የክልሉ መንግሥት ሁሉም ስራዎች በምርምርና ጥናት እንዲሁም በፋይናንስ ድጋፍና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በቅልጥፍናና ጥራት እንዲከናወኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ጉባዔው የተለያዩ ዓዋጆችና ሹመቶችን በማጽደቅ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም