የተጀመረው አገራዊ ለውጥ እንዳይደናቀፍ የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ገለፁ

60
አዲስ አበባ  ጥቅምት 10/2011 በኢትዮጵያ የተጀመረው አገራዊ ለውጥ እንዳይደናቀፍ የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የተፎካከካሪ ፓርቲ አመራሮች ገለፁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከቀናት በፊት የመንግስታቸውን ዓመታዊ የሥራ ዕቅድ በተመለከተ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የተጀመረው አገራዊ ለውጥ እንዳይደናቀፍ የህዝብ ድጋፍ እንዳይለይ ጥሪ አቅርበው ነበር። ይህንን ጥሪ አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች የተጀመረው አገራዊ ለውጥ እንዳይደናቀፍ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል። የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት /ኢዴህ/ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ ፤ መላው ህዝብ ለውጡ እንዲፋጠንና እድገት እንዲመጣ ሁሉም በየፊናው የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት መስራት አለበት ይላሉ።  የለውጥ እንቅስቃሴውን ተከትሎ ተጀመሩ የተግባር ሥራዎች መሬት መውረድ አለባቸው የሚሉት ደግሞ  የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ናቸው። ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ለውጡን ከሚመሩት ባለፈ እታች ድረስ መዝለቅና ሁሉም ከልቡ ሊቀበለው ይገባል ይላሉ። በቅርቡ ወደአገር ቤት የተመለሰው የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ  /ኢሕአፓ/ ቃል አቀባይ ኢንጂነር ሰለሞን ገብረስላሴ በበኩላቸው፤ ፓርቲያቸው የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር  አካሄድን ቅድሚያ በመስጠት የተጀመረው አገራዊ ለውጥ እንዳይደናቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢዴፓ/ ፕሬዚደንት ዶክተር ጫኔ ከበደ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግስት የአሰራር እንቅስቃሴ ውስጥ የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችል የማማከር ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ይናገራሉ። ፓርቲዎቹ ለአገራዊ ለውጡ መሳካት የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ እና ከመንግስት ጎን ለመቆም ዝግጁ መሆናቸውንም ጭምር ነው  የገለፁት።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም