ከበርበሬ ልማት የተሻለ ምርት እንጠብቃለን - የምእራብ ጎጃም አርሶ አደሮች

196
ባህር ዳር ጥቅምት 10/2011 የምርት ማሳደጊያ ግብዓትና ምርጥ ዘር ተጠቅመው ካለሙት በርበሬ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ አስተያየታቸውን የሰጡ የምዕራብ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ። በዞኑ ባለፈው የመኸር ወቅት በበርበሬ ከለማው 29 ሺህ 300 ሄክታር የሚጠጋ መሬት 670 ሺህ ኩንታል የበርበሬ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል። በጃቢጠህናን ወረዳ የጎርፍ ቀወንችን ቀበሌ አርሶ አደር ተፈራ መለሰ ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮው የመኽር ወቅት በአንድ ሄክታር መሬት ማዳበሪያ በመጠቀም እያለሙት ያለው የበርበሬ ሰብል ቡቃያው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል። የባለሙያን ምክረ ሃሳብ መሰረት አድርገው ግብዓትና የተሻለ ምርት በሚሰጥ የበርበሬ ዘር ተጠቅመው በማልማታቸው ከ20 ኩንታል በላይ ምርት አገኛለሁ ብለው እንዲጠብቁ ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት ለአንድ ሄክታር ያልሞላ ማሳቸውን በበርበሬ አልምተው ካገኙት ምርት ሽያጭ ከ93 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል። በርበሬ በገበያ ተፈላጊ ሰብል በመሆኑ የተሻለ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በዞኑ ቡሬ ዙሪያ ወረዳ የአዴል አጋታ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አለሰው ደመላሽ ናችው። በአንድ ሄክታር የእርሻ ማሳቸውን የተሻለ ምርት በሚሰጥ ዘር በማልማታቸው የበርበሬ ሰብሉ የዛላ አያያዝ በጥሩ ሁኔታ ላይ በመሆኑ እስከ 30 ኩንታል ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ አመልክተዋል። ካለፉት ሰባት ዓመት ጀምሮ በርበሬ በገበያ የተሻለ ዋጋ እያወጣ ከመጣ ወዲህ ትኩረታቸውን ወደ በርበሬ ልማቱ በማድረግ በየዓመቱ ከ30 እስከ 90 ሺህ ብር ገቢ እያገኙ መሆኑን ጠቁመዋል። የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ግብዓቶች በወቅቱ ገዝተው በመጠቀም በሚያገኙት የተሻለ የበርበሬ ምርት ኑሯቸውን በማሻሻል ልጆቻቸውን ማስተማር ችለዋል፡፡ በምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ ተወካይ አቶ አምራቹ  እንደገለጹት በዘንድሮው የመኽር ወቅት በዞኑ 29 ሺህ 298 ሄክታር መሬት በበርበሬ ሰብል እየለማ ይገኛል። አርሶአደሩ የበርበሬ ምርትን በጥራት አምርቶ ይበልጥ እንዲጠቀም በግብርና ባለሙያዎች ተገቢ የሆነ ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገለት እንደሚገኝ ተናግረዋል። ከክረምቱ መግቢያ ጀምሮም እስካሁን በዞኑ የተስተካከለ የአየር ፀባይና ተስማሚ የዝናብ ስርጭት በመኖሩ የበርበሬ ሰብል በተሻለ ቁመና እንዲገኝ አስችሎታል ብለዋል። በምርት ዘመኑ በበርበሬ ልማት እየተሳተፉ የሚገኙ 167 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮችም እያለሙት ካለው የበርሬ ሰብል ከ670 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል። ባለፈው ዓመት በዞኑ በበርበሬ ሰብል ከለማው ከ29 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከ622 ሺሀ 900 ኩንታል የሚበል ጥ ምርት ተገኝቷል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም