የተሻሻለ የማሽላና የሩዝ ዝርያ በመጠቀማችን የተሻለ ምርት እንጠብቃለን ፡- አርሶ አደሮች

75
ሽሬ እንዳስላሴ ጥቅምት 9/2011 ከሽሬ ማይፀብሪ የእርሻ ምርምር ማእከል በምርምር የወጣ ምርጥ የማሽላና የሩዝ ዝርያ በመጠቀማቸው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ በትግራይ ሰሜናዊ ምእራብ ዞን አርሶ አደሮች ገለፁ። በማእከሉ ተባዝተው ለአርሶ አደሩ የተሰራጩ ምርጥ ዝርያዎች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የመስክ ጉብኝት ተካሄዷል። ማሳቸው ከተጎበኘላቸው አርሶ አደሮች መካከል በሰሜን ምእራብ ዞን በታህታይ አዲያቦ ወረዳ ‘‘መንጠብጠብ‘‘ የተባለ የገጠር ቀበሌ ነዋሪ ግንባር ቀደም አርሶ አደር ሰሎሞን ብርሃነ አንዱ ናቸው። አርሶ አደር ሰሎሞን እንዳሉት ከሽሬ-ማይጸብሪ እርሻ ምርምር ማእከል የወሰዱትን  “ደቀባ” የተባለ ምርጥ የማሽላ ዘር ተጠቅመው የያለሙት ማሳ ቁመና በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ በምርጥ ዘሩ ከተሸፈነው አንድ ሄክታር ማሳ ከ50 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚያገኙ እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡ ይህም ቀደም ሲል የአካባቢ ዘር በመጠቀም ያገኙት ከነበረው የማሽላ ምርት ከ20 ኩንታል በላይ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ የዚሁ የገጠር ቀበሌ ነዋሪ ሴት አርሶ አደር  ልእልቲ በላይ በበኩላቸው ምርጥ ዘሩን ተጠቅመው ያለሙት ማሳ በእህል አያያዙ ካለፉት የምርት ወቅቶች የሚበልጥ አዝመራ በማሳቸው ለመመልከት በቅተዋል። ቀደም ሲል የአካባቢ የማሽላ ዘር በመጠቀም ከ28 ኩንታል የበለጠ ምርት አግኝተው እንደማያውቁ የገለፁት አርሶ አደሯ በዘንድሮው የምርት ዘመን በ22 ኩንታል የሚበልጥ ምርት አገኛለሁ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ፀለምት ወረዳ ልዩ ስሙ ‘‘መድሃኒአለም‘‘ በተባለ የገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ንጉሰ ታየ ከምርምር ማእከሉ የተገኘ “ማይፀብሪ አንድ” የተባለ  ምርጥ የሩዝ ሰብል ተጠቅመው ካለሙት ግማሽ ሄክታር ረግረጋማ የሩዝ ማሳ 15 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ገልፀዋል፡፡ ለምንም አይሆንም ብለው ለዓመታት ሳይጠቀሙበት የቆዩት ይሄው ረግረጋማ ማሳ  ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ከምርምር ማእክሉ ባገኙት የሩዝ ሰብል ምርጥ ዘር መሸፈን በመጀመራቸው  ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ችሏል። ሌላው የዚሁ ገጠር ቀበሌ ነዋሪና የሩዝ ምርት ተጠቀሚ አርሶ አደር ሽሻይ ሃይለማርያም በበኩላቸው ከምርምር ማእከሉ ጋር በፈጠሩት የጠበቀ ግንኙነት ፆም ያድር የነበረ ረግረጋማ ማሳ በሩዝ ሰብል በመሸፈን ከፍተኛ ገቢ እያገኙበት ነው። የሽሬ- ማይፀብሪ የእርሻ ምርምር ማእከል ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ደስታ በዚህ ጊዜ እንዳሉት በሄክታር እስከ 55 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችለውና ‘‘ደቀባ‘‘ የተባለው ምርጥ የማሽላ ዘር ማእከሉ በ75 ሄክታር መሬት ላይ እያበዛ ነው። ማእከሉ በቀጣይ የምርት ዘመን ምርቱን ለሚፈልጉ አርሶ አደሮች በስፋት ለማሰራጨት የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም