የኦሮሚያ ልማት ማህበር በሰሜን ሸዋ ዞን የልማት ኘሮጀክቶችን በማካሄድ ላይ ነው

46
ፍቼ ጥቅምት 9/2011 በኦሮሚያ ልማት ማህበር የሰሜን ሸዋ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በተያዘው ዓመት በ18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ መጀመሩን አስታወቀ። ቅርንጫፉ ለ13 ወረዳ የማህበሩ አስተባባሪዎችና ተወካዮች ለሁለት ቀናት ያዘጋጀው የስራ ግምገማ መድረክ በፍቼ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የጽህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ዋቅጅራ እንደገለጹት 56 የልማት ፕሮጀክቶቹ ግንባታ የተጀመረው በውጫሌ፣ አቢቹና ኩዩ የገጠር ወረዳዎች ነው። በወረዳዎቹ እየተሰሩ ካሉት መካከል 23 ምንጭ ማጐልበት ፣12 መካከለኛ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮና ጤና ኬላ ይገኙበታል። ለልማት ስራዎቹ የአካባቢው ሕብረተሰብ 700 ሺህ ብር ከማዋጣቱ ባሻገር የጉልበት ተሳትፎ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል። እንደ አቶ ተስፋዬ ገለፃ ሁሉም ፕሮጀክቶች በዓመቱ መጨረሻ ሲጠናቀቁ ከ20 ሺህ የሚበልጥ የህብረተሰብ ክፍል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሆናል። በፍቼ ከተማ እየተካሄደ ያለው የሩብ በጀት ዓመት አፈፃጸም ግምገማ ዋና ዓላማ የማሕበሩ አባላትና ደጋፊዎች የሚያደርጉትን የገንዘብ፣ የቁሳቁስና የእውቀት ተሳትፎ በቀጣይ ጊዜያት ማጠናከር በሚቻልበት ስልት ላይ ለመምከር መሆኑ ተመልክቷል። እንዲሁም አዳዲስ የገቢ ማስገኛ ኘሮግራሞችን በማዘጋጀት የማህበሩን አቅም ለማጠናከር ጭምር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ማህበሩ ዘንድሮ በዞኑ ዋና ዋና ከተሞች የገቢ ምንጩን ለማስፋት የሚያስችሉ የባዛር፣ ኪነ-ጥበብና የጨረታ መርሃ ግብር የሚያካሂድ ሲሆን ህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። የማህበሩ የኩዩ ወረዳ ተወካይ አቶ ሽፈራው ዋርሶ በሰጡት አስተያየት የልማት ስራዎችን ለማጠናከር የመንግሥት ሰራተኞችን፣ መምህራን፣ አርሶ አደሮችንና ነዋሪዎችን በማስተባበር እየሰሩ መሆኑን  ገልጸዋል። የግራር ጃርሶ አስተባባሪ አቶ ኮቱ ደምሴ በበኩላቸው ማህበሩ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠት የሚያከናውናቸው ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸው ዘንድሮም ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም