በቡና ልማትና ገበያ የተሰማሩ ሴቶች ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ተባለ

64
አዲስ አበባ ጥቅምት 9/2011 ኢትዮጵያ ውስጥ በቡና ልማትና ገበያ የተሰማሩ ሴቶች ለዘርፉ እድገት የበኩላቸውን ሚና መጫወት ይችሉ ዘንድ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ተባለ። በኢትዮጵያ ከ15 ሚሊዮን በላይ የሚልቀው ህዝብ ህይወት የተመሰረተው በቡና ልማትና ገበያ ሥራ ላይ ሲሆን ከዚህ ወስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ከዘረፉ የግብርና ምርት ጀምሮ እስከ ማቀነባበሪያና ንግድ ሥራዎች ድረስ ቁልፍ ሚና ያላቸው  እነዚህ ሴቶች ግን በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ድጋፍ እየተደረገላቸው አይደለም ሲል የኢትዮጵያ በቡና ላይ የተሰማሩ ሴቶች ማህበር  አስታውቋል። የማህበሩ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ እመቤት ታፈሰ ለኢዜአ እንደገለጹት በቡና ልማትና ገበያ ለተሰማሩት ሴቶች ድጋፍ ማድረግ በአገራዊው ምጣኔ ኃብት ውስጥ ጉልህ ድርሻ ላለው የዘርፉ እድገት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። ያም ሆኖ ግን  በዘርፍ ለተሰማሩ ሴቶች የስልጠና፣ የፋይናንስ፣ የገበያ ፍለጋና ሌሎች ድጋፎች በስፋትና በተደራጀ መልክ እየተሰጠ አይደለም። እንደ ወይዘሮ እመቤት ገለጻ በቡና ምርት ላይ አብዛኛው ስራዎች የሚከናወኑት በሴቶች ጉልበት ቢሆንም ተጠቃሚነታቸው አነስተኛ ነው። ሴቶች በተሰማሩበት የቡና ልማትና ገበያ ሥራ ጥቅም እንዲያገኙ ለማስቻልና የዘርፉን ንግድ ለማጠናከር ፋይናንስን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን በተቀናጀ መንገድ ለሴት የዘርፉ ተሳታፊዎች መስጠት እንደሚገባ ነው የማህበሩ ፕሬዚዳንት የተናገሩት። በመላው አገሪቱ ከሚገኙ የቡና አምራች ሴቶች ጋር ትስስር በመፍጠሩ ረገድም በተለይ ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ገበያ ልማት ባለስልጣን ድጋፍ እንደሚፈልጉም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር በበኩላቸው በማህበሩ የተጠቀሱትን ችግሮች በመቅረፍ በዘርፉ የተሰማሩ ሴቶችን መደገፍ እንዲቻል ጥናት እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ። በዘርፉ የተሰማሩ ሴቶች ለማበረታትና ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሻፊ የሴቶችን አቅም ለማጠናከርም ከተለያዩ መንግስታዊ  ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀው የቡና ግብይት ጥራትና ቁጥጥር አዋጅ 1051 የማስፈጸሚያ ደንብ በተለይም የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። ይኸውም የሴቶችን ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባለፈ ሴቶች ጥራት ያለው ቡና በማምረት በኩል ውጤታማ በመሆናቸው የአገሪቱ ቡና በዓለም የተሻለ ዋጋ እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑንም ነው ያመለከቱት። በቀጣይም የሴቶችን አቅም በመገንባትና ትስስር የመፍጠር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ቡና አምርተው ወደ ውጭ ለመላክ ፍቃድ ያወጡ ሴት የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ቁጥር 45 መሆኑን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። "የኢትዮጵያ በቡና ላይ የተሰማሩ ሴቶች ማህበር" 2009 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን  በቡና ምርት፣ እሴት በመጨመር በአቅራቢነትና ወደውጭ በመላክ ከተሰማሩ ሴቶች ጋር ትስስር በመፍጠር በጋራ የሚሰራ ነው። ማህበሩ የዓለም አቀፉ ሴት ቡና አምራቾች ህብረት (ኢንተርናሽናል ውሜን ኮፊ አሊያንስ) አባልም ነው። አባላቱ ስልጠናን ጨምሮ አለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ዕውቅና እና በውጭ አገራት በንግድ ትርዒቶች የመሳተፍ ዕድል እንዲያገኙ አድል እየተፈጠረላቸው ነው ተብሏል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም