የመሬት ይዞታ ባለቤትነታችን በመረጋገጡ ተጠቃሚ ሆነናል... የሰሜን ሸዋ አርሶ አደሮች

254
ደብረ ብርሃን ግንቦት 14/2010 በመንዝ ማማ ምድር ወረዳ ፍሬሰላም ቀበሌ 16 ነዋሪ ናቸው አርሶ አደር የሸዋእመቤት ተሾመ። እንደዛሬ ሳይሆን የመሬት ባለቤትነት መብታቸው ባልተከበረበት ወቅት መሬታቸውን በአግባቡ ለመጠቀም ተቸግረው ቆይተዋል። ባለፉት ዓመታት ግንዛቤያቸው በማደጉ ለመሬታቸው በተሰጠው እውቅና ለሰባት የተለያዩ የእርሻ ማሳዎቻቸው ካርታ ተሰርቶላቸው የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር መያዛቸውን ነው የገለጹት። አርሷደሯ እንዳሉት የመሬት ባለቤትነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ መሬታቸውን በራሳቸው በማረስ፣ በማከራየት እንዲሁም ከባለ ሀብት ጋር አቀናጅቶ በማሳረስና መብታቸውን ለሌላ በማውረስ ተጠቃሚ  ሆነዋል። “መንግስት ባለፉት ዓመታት ሴቶች የመሬት ባለቤት እንዲሆኑ ያደረገው ጥረት ፍሬያማ ስለመሆኑ እኔ አንድ ማሳያ ነኝ” ያሉት አርሶአደር የሸዋእመቤት በቀጣይ መሬታቸውን አስይዘው በመበደር የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀምና የንግድ ሥራ ለመጀመር አቅደው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል። የአርሶ አደሮችን የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጥና ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ማስጠበቅ የተቻለው ከግንቦት 20 ድል ማግስት እንደሆነ የገለጹት ደግሞ በመንዝ ቀያ ወረዳ ቀበሌ 07 ነዋሪ አርሶ አደር ወልደአረጋይ ወልደሚካኤል ናቸው። የእርሻ መሬታቸው በካርታ ተወስኖ መሰጠቱ የመሬቱን ለምነት በባለቤትነት ለመጠበቅና ምርታማነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ እንደረዳቸው አመልክተዋል። "መንግስት የመሬት ባሌትነት እንዲረጋገጥ ማድረጉ በመሬት ይገባኛል ይደርስ የነበረውን የእርስ በእርስ ግጭቶች በማስቀረት ፍቅርንና መከባበርን በማጎልበት ለጋራ እድገት ተባብረን እንድንሰራ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል” ብለዋል። " ቀደም ሲል ሴቶች በመሬታቸው ያፈሩትን ሀብት እንኳ ሳይቀር በወንዶች የመነጠቅና በመሬት ባለቤትነት የመጠቀም መብታቸው ተገፍቶ ይኖሩ ነበር” ያሉት ደግሞ የእዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ተዋበች በየነ ናቸው። "ባለፉት ዓመታት መብታችን በመከበሩ በመሬት የተነሳ አለመግባባት ሲፈጠር እንኳ በመደበኛ ፍርድ ቤት በተገቢው መንገድ ያለምንም ወጪ ተከራክረን መብታችንን ማስጠበቅ ችለናል" ብለዋል። እንደአርሶ አደር ተዋበች ገለጻ መንግስት ሴቶች የመሬት ባለቤትነታቸው ተረጋግጦ በነጻነት እንዲጠቀሙ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ በእርሻ ማሳቸው ኢኮኖሚካል ጠቀሜታ ያላቸውን ዛፎች በመትከል ገቢያቸውን ይበልጥ ለማሳደግ አግዟቸዋል። በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የገጠር መሬት አስተዳደረና አጠቃቀም መምሪያ የገጠር መሬት አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ቀነአ ጋዲሳ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት የመሬት አያያዝን ለማስተካከል በተሰራው ሥራ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል። ህገ መንግስቱ የመሬት ተጠቃሚዎችን መብት በላቀ ደረጃ ለማስከበር በባህላዊ መንገድ ተመዝግቦ የነበረውን መሬት የአየር ካርታ በማስነሳት ተጠቃሚዎች ባለቤትነታቸው እንዲረጋገጥ መብት መስጠቱንም አመልክተዋል። በእዚህም ቀደም ባሉ ዓመታት በዞኑ በ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ማሳ ላይ ተጠቃሚ ለነበሩ 451 ሺህ 742 ባለይዞታዎች የመጀመሪያ ደረጃ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር እንዲሰጥ መደረጉን ነው የገለጹት። በአሁኑ ወቅትም በዞኑ ሰባት ወረዳዎች ባለይዞታዎች በአካል ተገኝተው በሚያረጋግጡት መሰረት መሬት የመለካት ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን በሌሎች አምስት ወረዳዎች የልኬት ሥራ እየተከናወነ ነው። በተጨማሪም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተደገፈ መንገድ መሬቱን እንደገና በመለካት ቋሚ ማመላከቻና የማሳ ዝርዝሮች ተሟልቶላቸው ለ67 ሺህ 700 ባለይዞታዎች 332 ሺህ 947 መሬቶች የማሳ ካርታ እንዲሰጥ መደረጉን ተናግረዋል። የአርሶ አደሮችን የመሬት ባለይዞታነት እንዲረጋገጥና ህገ መንግስታዊ መብታቸውን እንዲጠበቅ ማድረግ የተቻለው በግንቦት 20 ድል በመሆኑ ለቀኑ የተለየ ትኩረት እንዳላቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም