መገናኛ ብዙሃን ወቅታዊና አዳዲስ መረጃዎችን በፍጥነት በማድረስ ህብረተሰቡን ከተሳሳቱ መረጃዎች ሊጠብቁ ይገባል---ነዋሪዎች

84
ጥቅምት9/2011የመገናኛብዙሃን ወቅታዊና አዳዲስ መረጃዎችን በፍጥነት በማድረስ ህብረተሰቡን ከተሳሳቱ የማሃበራዊ ሚዲያ መረጃዎች መጠበቅ እንዳለባቸው በመዲናዋ የሚገኙ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ተከትሎ የሃገራችን የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የህብረተሰቡን ቁልፍ ችግሮች በማጋለጥ የተሻለ እንቅስቃሴ ቢኖርም ወቅታዊና አዳዲስ መረጃዎችን በፍጥነት በማድረስ በኩል ክፍተቶች እንደሚስተዋልባቸው አስታውቀዋል፡፡ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የአስኮ የህዝብ ቤተ-መጽሃፍት አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ቦጋለ መገናኛ ብዙሃን ከዚህ በፊት ወገንተኝነት ባደላ መልኩ ያከናውኑ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን የህብረተሰቡን ጥያቄና ችግር ያለአንዳች ተፅዕኖ ማቅረብ በመጀመራቸው መሻሻሎች ታይተዋል፡፡ የመገናኛ ብዙሃን መረጃን በጥንቃቄና በፍጥነት ለህዝብ ጆሮ ባለማድረሳቸው ምክንያት ባልተረጋገጠ መረጃ ላይ ወደሚንቀሳቀሱ ማህበራዊ ሚዲያዎች በመሄድ ለሃሰተኛ የማሃበራዊ አጀንዳዎች ሲዳረጉ እንደሚስተዋሉም አስታውቀዋል፡፡ የመንግስት ሰራተኛና የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ አዛለች በላይነህ በበኩላቸው ከዚህ በፊት መረጃ ለማግኘት የውጭ ሚዲዎችን እንደሚመለከቱና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የአገር ውስጥ ሚዲያዎች መሻሻል በማሳየታቸው የሃገር ውስጥ ሚዲያዎችን መመልከት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ መገናኛ ብዙሃን የህብረተሰቡን ችግር በማውጣትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማሳየት ለዲሞክራሲ ስርአቱ ማበብ የበኩሉን ሚና ሊጫወት ይገባል ያሉት ወይዘሮ አዛለች፤ ችግሮች ሲፈጠሩ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ማሰራጨት ይኖርባቸውም ብለዋል፡፡ መረጃን በፍጥነት ለህዝብ አለማድረስ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝንም ነው የጠቀሱት። ከቅርብ ወራት በፊት የመገናኛ ብዙሃን ግልፀኝነት ይጎድለው እንደነበርና አሁን የተጀመረውን  ለውጥ መሰረት አድርጎ በሚዲዎች የታየው መነቃቃት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ያለው ደግሞ በቀለምወርቅ መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚኒሚዲያ አስተባባሪ ተማሪ ታምራት ተርፈ ነው፡፡ የጂባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ያሲን ከድር በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን መረጃን ለህብረተሰቡ በፍጥነት በማድረስ በኩል የሚያሳዩት ትጋት ጥሩ ቢሆንም አሁንም በበቂ ሁኔታ እየሰሩ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ወቅታዊና አዳዲስ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያው ከተናፈሱ በኋላ ስለሚገለጽ ህብረተሰቡ ከሚዲያው ይልቅ ማህበራዊ ድረ-ገፆችን በመከተል ወደተሳሳተ መንገድ የማምራት ሁኔታ የሚስተዋል በመሆኑ ሊስተካከል ይገባልም ብለዋል፡፡ በአንዳንድ ሚዲያዎችም የጋዜጠኝነት ስነምግባር ከሚጠይቀው ውጭ ሚዛናዊነት በጎደለው ሁኔታ የሚቀርቡ ዘገባዎችና ፕሮግራሞች መኖራቸውን የገለጹት መምህር ያሲን በተለይ ህብረተሰቡን ለግጭት የሚዳርጉ ዘገባዎች እንዳይቀርቡ ተቋማቱ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የፕሬዘዳንቱን ሞሽን ለማብራራት በትናንትናው እለት ህዝብ ተወካች ምክር ቤት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰጡት ማብራሪያ ከማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን ለማስወገድና ስርዓት ለማበጀት የህግ ስርዓት እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አፍራሽና አጥፊ ተግባራትን ለመቆጣጠርና ትክክለኛ መረጃ በፍጥነት ማድረስ አንደኛው መፍትሄ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዓመቱ አንኳር አጀንዳዎች አንዱ የሚዲው አሰራር እንደሆነም መጠቆማቸው ይታወሳል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም