የጅማ ዞን ነዋሪዎችና የመንግስት ሠራተኞች ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

58
ነቀምቴ ጥቅምት 8/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢዎች ለሚገኙ ዜጎች የጅማ ዞን ነዋሪዎችና የመንግስት ሠራተኞች የምግብና የአልባሳት ድጋፍ አደረጉ። የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱል ሐኪም ዕርዳታውን ለምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሲያስረክቡ እንደገለጹት ድጋፉ የተደረገው የዞኑ ሕዝብና የመንግስት ሠራተኞች ባደረጉት ትብብር ነው። በእርዳታውም ግምቱ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ነው የገለጹት። ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲደርስ የተደረገው 700 ኩንታል የስንዴ ዱቄት፣ 200 ኩንታል ማካሮኒ፣ ጫማዎች፣ የተለያዩ አልባሳት፣ መድኃኒቶች እና የተለያዩ ቁሳቁሶች ናቸው። የዞኑ ነዋሪዎችና የመንግስት ሠራተኞች የሚያደርጉትን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አቶ አብዱል ተናግረዋል። የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ በቀለ በበኩላቸው ዕርዳታውን በተረከቡበት ወቅት እንደገለጹት የጅማ ዞን ሕዝብና የመንግስት ሠራተኞች ላደረጉት ድጋፍ አምስግነዋል። በተለይ ካሉበት አካባቢ ሩቅ መንገድ ተጉዘው ለተፈናቀሉ ወገኖቻቸው ፈጥነው በመድረሳቸው በራሳቸውና በምሥራቅ ወለጋ ዞን ሕዝብ ስም ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም