ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥቅምት 21 በጀርመን ፍራንክፈርት በአውሮፓ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር ይወያያሉ

141
አዲስ አበባ ጥቅምት 8/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ በአውሮፓ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ አባላት ጋር ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም ውይይት ያደርጋሉ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያደርጉት ጉብኝትና ውይይት "አንድ ሆነን እንነሳ ነገን እንገንባ" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ሲሆን በውይይቱ ከ20 እስከ 25 ሺህ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ጉብኝቱ ሁሉም ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን በፍቅር እንዲገነቡ የሚያስችል በመሆኑ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ገልጸዋል። በአጠቃላይ የሚደረገው ጉብኝትና ውይይት ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲና በውጭ ግንኙነት ላይ የሚሰራው ስራ አካል እንደሆነ ተገልጿል። ቃል አቀባዩ ይህ ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ቤተሰብ በሚያገናኘው የፍራንክፈርት ውይይት ስኬታማ እንዲሆን በአገር ውስጥም ከአገር ውጪም አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል። በአገር ውስጥ ያለውን ዝግጅት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የሚመራና ታዋቂ ግለሰቦች፣ ባለሃብቶች እንዲሁም ሌሎች አባላት ያሉበት ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቋሞ ዝግጅቱን እያስተባበረ መሆኑን ተናግረዋል። ኮሚቴው ባላፉት ሳምንታት ውይይቱ ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። ኮሚቴው በቅርቡ በአውሮፓ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች ጋር በፍራንክፈርት ስብስባ በማድረግ የእቅድ ስራ ግምገማ ማከናወኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ፤ በአውሮፓ ከሚገኙ 13 የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና የቆንስላ ጽህፈት ቤት የቅድመ ዝግጅት ሂደቱ ስኬታማ ሆኖ መቀጠሉን ተናግረዋል። በጀርመን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲና ፍራንክፈርት የሚገኘው ቆንስላ ጽህፈት ቤት የአስተባባሪነት ሚናቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። በአውሮፓ የሚገኙ ሁሉም ሚሲዮኖች በየአገሩ ባሉ አምባሳደሮች የሚመራ ኮሚቴ በማቋቋም ለውይይቱ ውጤታማነት ጥረት እያደረጉ እንደሆነም አስታውቀዋል። በውይይቱ ላይ በአካል መገኘት የማይችሉ በስልክ፣ ኢሜይልና በማህበራዊ ሚዲያ ጥያቄና አስተያየቶቻቸውን ለፍራንክፈርት ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት እንዲያቀርቡ መደረጉን አቶ መለስ ጠቁመዋል። ውይይቱ ዳያስፖራዎቹ በኢትዮጵያ በተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በሚኖራቸው አስተዋፅኦ ላይ ጥያቄያቸውንና ፍላጎታቸውን በማቅረብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሀሳብ የሚለዋወጡበት እድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል። ከሶስት ወር በፊት በሰሜን አሜሪካ (ዋሽንግተን፣ ሎስአንጀለስ እና ሚኒሶታ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” በሚል ርዕስ በርካታ ኢትጵያውያንን ያሳተፈ ታሪካዊ  ውይይት ማካሄዳቸውን አቶ መለስ አስታውሰዋል። ለዓመታት የነበረው የልዩነት ግንብ ፈርሶ የህብረት፣ የይቅር ባይነትና የፍቅር ድልድይ መገንባቱን ጠቁመው ይሄው ተጠናክሮ በፍራንክፈርት መድረክም እንደሚደገም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በአዲስ የፖለቲካ ድባብ እንዲሁም በአዲስ የመነቃቃት የይቅርባይነት፣ በአንድነትና በህብረት ውስጥ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደምትገኝ ነው አቶ መለስ ያስረዱት። ''ባለው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የአገር ውስጥ ህዝብን ብቻ ይዞ መሄድ በአንድ እጅ ማጨብጨብ እንደሆነና 3 ሚሊዮን የሚጠጋ የዳያስፖራ ማህበረሰብ ያላሳተፈ የአገር ግንባታ ስኬታማ ሊሆን አይችልም'' ብለዋል። በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በቀጣዩ ሳምንት ማገባዳጃ በፈረንሳይና በጀርመን የስራ ጉበኝት እንደሚያደርጉ ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ከፈረንሳይ ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮንና ከጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ተናግረዋል። ዶክተር አብይ ጉብኝቱን የሚያደርጉት ከአገሮቹ መሪዎች በቀረበላቸው ግብዣ መሰረት እንደሆነም አቶ መለስ አስረድተዋል። ባለፋት ቀናት የነበሩ ጉብኝቶች የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ስራ ማጠናከሩንና አገሮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት እንዲጠናከር የሚያሳዩት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን እንደሚያመላክት አብራርተዋል። በቅርቡ የጣልያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ፣ የስሎቬኒያ ፕሬዚዳንት ቦሩት ፓሆርና የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያ መጎብኘታቸው የሚታወስ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም