በምዕራብ ሸዋ ዞን 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የቡና ችግኝ ተዘጋጅቷል

3684

አምቦ  ግንቦት 14/2010 በምዕራብ ሸዋ ዞን በዘንድሮው የክረምት ወራት የሚተከል 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የቡና ችግኝ መዘጋጀቱን የዞኑ ቡና፣ ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን   አስታወቀ ።

በቡና ችግኝ ዝግጅቱ  ለ670 ወጣቶች የስራ እድል ተፈጥሯል።

በዞኑ ቡና፣ ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን   የቡና ልማት ስራ ባለሞያ አቶ ደጀኔ ደቡሼ እንዳሉት  የቡና ችግኙ የተዘጋጀው በ658 ጣቢያዎች ነው፡፡

የተዘጋጀው ችግኝም በመጪው ክረምት በዞኑ 13 ወረዳዎች በሚገኝ 900 ሔክታር መሬት ላይ ለመትከል የጉድጓድ ዝግጅት መጀመሩን ገልፀዋል፡፡

ዞኑ በዋነኛነት የእህል ሰብሎች አምራች ቢሆንም ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ  በወረዳዎቹ የቡና ልማት እየተስፋፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮ የሚተከለው ችግኝ የዞኑ በቡና የሚለማውን መሬት ሽፋን ከ19 ወደ 23 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ  ያደርገዋል ተብሎ  ይጠበቃል፡፡

በቡና ችኝ ዝግጅቱ በቡድን የተደራጁ 670 ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩንም ገልፀዋል፡፡

በችግኝ ዝግጅት ከተሳተፉ አርሶአደሮች መካከል የዳኖ ወረዳ ወጣት ቢሊሱማ መጫ በሰጠው አስተያየት ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን 25 ሺህ የቡና ችግኝ አዘጋጅተው እንክብካቤ እያደረጉ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የባኮ ወረዳ አርሶአደር ፊጡማ ለታ በበኩላቸው  በመጪው ክረምት የሚተከል 20 ሺህ የቡና ችግኝ በማዘጋጀት የጉድጓድ ቁፋሮ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአንድ ሄክታር መሬት ላይ 8 ሺህ ጉድጓዶችን ቆፍረው ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢሉ ገላን ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር ሙለታ ተሰማ እንዳሉት በግላቸው 12 ሺህ የቡና ችግኝ ለመትከል ጉድጓድ አዘጋጅተው የተከላውን ጊዜ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ ባለፈው አመት ከተተከለው  2 ነጥብ 1 ሚሊየን የቡና ችግኝ ውስጥ  68 በመቶ መጽደቁ ታውቋል፡፡