በአገሪቱ የተፈጠረው ከፍተኛ የበጀት ጫና የደረጃ ማስተካከያ እና የደመወዝ ጭማሪ ማድረግ አላስቻለም-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

68
አዲስ አበባ ጥቅምት 8/2011 በአገሪቱ የተፈጠረው ከፍተኛ የበጀት ጫና ለፐብሊክ ሰራተኞችን የደረጃ ማስተካከያና የደመወዝ ጭማሪ ማድረግ እንዳላስቻለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ ርዕሰ ብሄር ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ላነሱት ጥያቄ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ "የፐብሊክ ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪና የደረጃ ማስተካከያ የት ደረሰ?" የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ ይነሳል። ባለፉት ዓመታት የአየር መዛባት ባስከተለው ድርቅ ምክንያት መንግስት አሁንም ድረስ ለበርካታ ዜጎች መሰረታዊ ፍላጎት እያሟላ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ለሜጋ ፕሮጀክቶች እና ለሌሎች ታላላቅ አገራዊ ልማቶት የተበደረችው ገንዘብ የመክፈያ ጊዜ መድረሱንም አክለዋል። "እነዚህና ሌሎች አገራዊ ሁነቶች የፈጠሩት የበጀት ጫና መንግስት ለፐብሊክ ሰራተኞች የደረጃ ማስተካከያ እና የደመወዝ  ጭማሪ እንዳያደርግ ጫና ፈጥሯል" ብለዋል። በቀጣይም የተፈጠረው የበጀት ጫና ሲስተካከል ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ ለፐብሊክ ሰራተኛው የደመወዝ ማሻሻያ እንደሚደረግም አክለዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም