ቦርዱ የ2012ቱን ምርጫ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ነፃና ፍትሃዊ ለማድረግ እየሰራሁ ነው አለ

58
አዲስ አበባ ጥቅምት 7/2011 በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ነፃና ፍትሃዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። አሰራሩን በማዘመን በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ነፃ፣ ግልጽና ቀልጣፋ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል አቅም እየገነባ መሆኑንም ለኢዜአ ገልጿል። የቦርዱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ተስፋለም አባይ የጽህፈት ቤቱን አሰራር በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል ብለዋል። ቦርዱን በቴክኖሎጂ የማዘመኑ ሥራ በምርጫ ሂደቱ የህዝቡን የስልጣን ሉዓላዊነት በማረጋገጥ በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደውን አገራዊ ምርጫ ስኬታማ ያደርገዋልም ነው ያሉት። በአሁኑ ወቅት የጽህፈት ቤቱን የውስጥ ኮሙኒኬሽን ሥራዎች ለማቀላጠፍ የኔትዎርክ ዝርጋታ፣ የዳታ ቤዝ ማሳደግና የዌብ ፖርታል ሥራዎች በብሔራዊ የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል። ቦርዱ የዚምባብዌን የኤሌክትሮኒክስ ምርጫ አሰራር መመልከቱን የገለጹት አቶ ተስፋለም በዘርፉ ቀደም ብለው መስራት የጀመሩ አገሮች በመኖራቸው ልምዶችን በመውሰድ የተሻለ አሰራር ለመዘርጋት ጥናት እየተካሄደ ነው ብለዋል። ጥናቱን መሰረት በማድረግም የ2012 ዓ.ም የመራጮች ምዝገባን በቴክኖሎጂ ለማከናወን የሚያስችል አሰራር እንደሚዘረጋ ጠቁመዋል። ቦርዱ አሰራሩንና ምርጫውን በቴክኖሎጂ ለማዘመን እየሰራ ቢሆንም በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ በቂ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ባለመኖሩ ምክንያት የድምጽ አሰጣጡ በኤሌክትሮኒክስ አይካሄድም ብለዋል። ቦርዱ ከቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችና ከ62ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባካሄዳቸው ውይይቶች የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላ፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ድምጽ አሰጣጥ የማካሄድ ክፍተትና የመዋቅር ችግሮችን በመለየት በጥናት የተደገፈ ምላሽ ለመስጠትም እየሰራ ነው። በተጨማሪም ቦርዱ ከዚህ ቀደም በተገቢው ሁኔታ ያልፈጸመውን የመራጮችና የስነ ዜጋ ትምህርት መስጠትን በተመለከተ ቀጣይነት ባለው መልኩ ተግባራዊ እንደሚደረግ አቶ ተስፋለም ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም አገር አቀፍ ምርጫ እንደምታካሂድ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም