በካቢኔው የሴቶች ተሳትፎ ከወንዶች ጋር መመጣጠኑ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ያጠናክረዋል

64
ነቀምት፣አምቦ፣ጊምቢ ጥቅምት 7/2011 በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ በተሰየመው ካቢኔ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ከወንዶች ጋር መመጣጠኑ የአገሪቱን ሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ያጠናክረዋል ሲሉ በኦሮሚያ ክልል የሦስት ከተሞች ነዋሪዎች ገለጹ። የነቀምቴ፣የአምቦና የጊምቢ ከተማ ነዋሪዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በካቢኔው የትምህርት ዝግጅት፣ ብቃት፣ ልምድና ቁርጠኝነትን መሠረት በማድርግና  የሴቶችን ተሳትፎ 50 በመቶ በመሆኑ  አስደስቷቸዋል። በሹመቱ ለሴቶች የተሰጠው ትኩረት የአገሪቱን ሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ  ወደ ላቀ ደረጃ ያሳድገዋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። በነቀምቴ ከተማ የ07 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሳዲያ አብዱልቃድር እንደሚሉት ሹመቱ የሴት አመራሮች ተሳትፎ በየደረጃው እንዲያብብ ያነሳሳል ብለዋል። ''ተሿሚዎቹ የተረከቡትን ሥልጣንና ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት አመርቂ ውጤት ያስመዘግባሉ" የሚል እምነት አለኝ ብለዋል። በከተማዋ የ03 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሽመልስ አምሳሉ በበኩላቸው ሴቶች የባህልና የወንዶች ተጽዕኖ ስለነበረባቸው የፖለቲካ ተሳትፎአቸውን አናሳ አድርጎ መቆየቱን አስታውሰው፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው ሹመት ሁኔታውን እንደሚለውጠው ገልጸዋል። ሌላዋ የህግ ባለሙያ ወይዘሮ አየለች ኦፍጋአ ሴቶች በብዛት ለከፍተኛ አመራርነት መብቃታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ ሚኒስትሮቹ ብልሹ አሠራርን የማምከን አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል። የአምቦ ከተማ በመንግሥት ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ወርቁ ሁንዴሣ እንደሚሉት መንግሥት የሴቶችን እኩልነት በፖለቲካ ተሳትፎ በተግባር ማረጋገጡ ይደነቃል። በሚኒስትር ደረጃ የተሰጠው ኃላፊነትም እስከታችኛው መዋቅር ሊወርድ ይገባል ባይ ናቸው። የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ መምህር ከተማ በዳሳ በአገሪቱ ሙስናን ለመከላከል እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ሴቶች እምብዛም በጥፋተኝነት እንደማይነሱ አውስተው፣መንግሥት ሴቶችን ለከፍተኛ አመራርነት ከማብቃት ባለፈ የአገርና የመንግሥትን ሀብት ከብክነትና ከምዝበራ እንደሚታደግ ጠቁመዋል። የአምቦ ከተማ የአገር ሽማግሌ አቶ ዋቁማ መረራ በበኩላቸው ሹመቱ የህዝቡን ፍላጎት ያገናዘበ፣ ፆታን፣ዕውቀትን፣ሙያንና ክህሎትን ማዕከል በማድረጉ የተሻለ ለውጥ ያመጣል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል። የጊምቢ ከተማ የዐ3 ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ አብዮት ሲሳይ ሴቶች በካቢኔው ያገኙት ሹመት እንደሚያስደስትና ሴት ሚኒስትሮቹ አገሪቱን ለዘላቂ ሰላም፣ ብልጽግናና ዕድገት እንደሚያበቁ እምነታቸው ገልጸዋል። ወጣት ቦንቱ ወርቅነህ የተባለች የዚሁ ከተማ ነዋሪ እንደምትለው ሴት ሚኒስትሮች የለውጥ ጉዞውን ለማሳካት በመንግሥትና በህዝብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ይወጣሉ ብዬ አስባለሁ ብላለች። የጊምቢ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ስመኝ ኪዳኑ በበኩላቸው ሴት ልጅ የብርታትና የትዕግስት ተምሳሌት ስለሆነች እድሉ ከተሰጣት ማንኛውንም ኃላፊነት በብቃት ትወጣለች ይላሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም