በኢትዮጵያ ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚያስተዋውቅ መድረክ በለንደን ተካሄደ

1575

አዲስ አበባ ጥቅምት 7/2011 በኢትዮጵያ ያሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለእንግሊዝ ባለሃብቶች የሚያስተዋውቅና ተሳትፏቸውን ማስፋት ዓላማ ያደረገ የኢትዮ-እንግሊዝ የቢዝነስ መድረክ በለንደን ተካሄደ።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ የኢኮኖሚ አማካሪ ዶ/ር አርከበ እቁባይ ከ30 በላይ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች የተካተቱበትን ልኡክ መርተው በመድረኩ የታደሙ ሲሆን ኢትዮጵያ ለኢንቨስተሮች የምታደርገውን ማበረታቻ ለተሳተፊዎች አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ  አካባቢያዊና አለምዓቀፍ ገበያዎች ተጋሪ በመሆኗ በኢትዮጵያ የተሰማሩ ሁሉም የውጭ ኢንቨስተሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን  ዶክተር አርከበ ገልፀዋል።

መንግስት የተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን የገለፁት ዶክተር አርከበ ለኢንቨስተሮች የበለጠ አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጠርና  እንግሊዛውያን ባለሃብቶቸ የጨርቃጨርቅ፣ የቆዳ ውጤቶች፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ማእድንና ኢነርጂን ጨምሮ በተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ሰፊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ዶክተር አርከበ እንዳሉት አገራችን ያለው ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት እ.ኤ.አ ከ2012 ጀምሮ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መሆኑንና መንግስት በ2025 ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚዋ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በመድረኩ  የእንግሊዝ ኩባንያዎች የተሳተፉ ሲሆን በኢትዮጵያ  የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው የሚገኙ የእንግሊዝ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ  ስላለው ምቹና አዋጭ የኢንቨስትመንት አማራጭ ምስክርነታቸውን መስጠታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡