መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በተገቢው መንገድ እየደረሰን አይደለም - የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች

101
ደብረ ብርሃን ጥቅምት7/2/2011 መንግስት ድጎማ የሚያደርግባቸው መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች  በተገቢው መንገድ  ሊደርሳቸው ባለመቻሉ መቸገራቸውን የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ። የሰሜን ሽዋ ዞን ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት ግብረሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡ በደብረብርሃን ከተማ የ06 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ፍቃዱ አሰፋ እንደገለጹት በመንግስት ድጎማ የተደረገባቸው ዘይት፣ ስኳርና ዱቄት በምደባቸው መሰረት በየወሩ ኮታቸው እየደረሳቸው ባለመሆኑ በኑሯቸው ላይ ጫና እያሳደረባቸው ነው። በየወሩ የሚመጣላቸውን ዘይትና ስኳር ከቀበሌያቸው ለመውሰድ  በሌሊት ወረፋ ቢይዙም ሳይደርሳቸዉ አለቀ እንደሚባሉ አስታውቀዋል፡፡ መንግስት በህገ-ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ምርቶችን በመቆጣጠር ለህዝቡ እንዲደርሱ መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ ሌላዋ የ02 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ በላይነሽ ማርቆስ ለህዝብ የሚመጡ የድጎማ ምርቶች በምደባቸው መሰረት ማግኘት ባለመቻላቸው ከነጋዴዎች ዋጋ ጨምረው ለመግዛት መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በየወሩ ያገኙት የነበረው ዘይትና ስኳር ሳይደርሳቸው አለቀ እንደሚባሉ የገለፁት አስተያየት ሰጪው በተለይ ስኳር ከነጋዴ አንዱን ኪሎ ከ40 ብር በላይ ለመግዛት መገደዳቸውን አስታውቀዋል፡፡ በሰሜን ሸዋ ዞን ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ የውጭ ድህረ ፍቃድ ኢንስፔክሽን ቡድን መሪ አቶ ዘነበ ክንፈ በበኩላቸው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው፡፡ በተደረገው ክትትልና ቁጥጥርም በተያዘው ዓመት ብቻ አንድ ሺህ 125 ኪሎ ግራም ስኳር፣  595 ሊትር ዘይት፣ አንድ ሺህ 400 ኪሎ ግራም የስንዴ  ዱቄት በህገ-ወጥ መንገድ ተከማችቶ መያዙን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም 5 ሺህ ሊትር ነዳጅ መያዙን አስታውቀዋል። በአጠቃላይ ከ139 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለውን ይህንኑ የፍጆታ ምርት አከማችተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው  በህግ እየታየ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ክስ ከተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች መካከል አራቱ እስከ 5 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣትና የሁለት ዓመት እገዳ በፍርድ ቤት ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ተናግረዋል። በየወሩ የሚመጣውን የፍጆታ ምርት በፍትሃዊ መንገድ ለህዝቡ ለማዳረስ በአዲስ መልክ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም