የሰላም ሚኒስቴር ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ለውጡን ለማስቀጠል ጉልህ ሚና ይኖረዋል

55
አዲስ አበባ ጥቅምት 7/2011  አዲሱ የሰላም ሚኒስቴር በአገሪቷ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ። በአዲስ መልክ ከተዋቀሩና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ከጸደቁ ተቋማት መካከል የሰላም ሚኒስቴር አንዱ ነው። ሚኒስቴሩ በአገሪቱ ብሎም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን ለማድረግ የተቋቋመ መሆኑ ተነግሯል። የአዲስ አበባ ነዋሪው አቶ ላዕከ መስፍን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የሰላም ችግር እየተስተዋለ መሆኑን ተከትሎ የሰላም ሚኒስቴር መቋቋሙ ጠቃሚ እንደሆነ ነው የተናገሩት። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሰላም እጦት ሳቢያ የሚታየውን የዜጎች ህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት አዲስ የተቋቋመው መስሪያ ቤት በዘላቂነት ሊፈታው እንደሚችል እምነታቸውንም ገልጸዋል። ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ብርቱሰው ከበደም በተለይ በሰላም እጦት ምክንያት ለጉዳት እየተዳረገ ላለው ወጣት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መቋቋም ተስፋ የሚሰጥ እንደሆነ ነው የገለጹት። ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል በትክክለኛው ጊዜ የተቋቋመ ነው ያለው ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪው ወጣት ዳንኤል ከበደ ነው። በትውልድ አእምሮ ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ በመሆኑ የሚፈጠሩ ግጭቶች እንደማይኖሩ ያለውን እምነትም ገልጿል። የመዲናዋ ነዋሪ ወይዘሮ ካሰች አበራ በበኩላቸው ሰላም ከሁሉም በላይ አስፈላጊ በመሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰላም ሚኒስቴር መቋቋሙ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካም ተሞክሮ ይሆናል ብለዋል፡፡ የሰላም ሚኒስቴር የብሄራዊ ደህነነት መረጃ አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህነነት ኤጀንሲ፣ የፋይናንስ ደህነነት መረጃ ማዕከል፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች መምሪያ፣ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች፣ ብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራርና የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ዓለም ዓቀፍ የሰላምና የልማት ኢንስቲትዩትን ስራ በበላይነት ይመራል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም